Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በአመዛኙ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ነው – የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ላይ በክልሉ ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች በአመዛኙ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በሰጠው መግለጫ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነው ተብሏል።

የፀጥታ ቢሮው ሃላፊ ደሳለኝ ጣሰው በህዝቡ ሲንከባለሉ የመጡ ጥያቄዎችን ወደጫፍ በመውሰድ ለግጭት የተጠቀሙ አካላት ክልሉ ላይ አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርገዋል ብለዋል።

ህብረተሰቡ እንዲፈቱለት የሚፈልጋቸው በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም በሰላምና በመነጋገር እንጅ በጦርነት እንደማያምን በተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ አንስቷልም ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ ግጭቱ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑና ከቀውስ አዙሪት መውጣት እንደሚገባ ማንሳቱንም ጠቅሰዋል።

ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰራ ባለው ስራም አሁን በአመዛኙ በክልሉ የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።

ትርፍ የሌለው እርስ በእርስ ያጋጨ ወንድማማቾች እንዲዋጉ ያደረገ ግጭት ነው ያሉት ሃላፊው፥ ይህ የሚያሳዝን ከፍተኛ ስህተት ውስጥ ያስገባ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።

ይህ ግጭት የማህበረሰቡ ችግር እንዳይፈታ ጊዜ የሚበላ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ፥ መንግስት ማንኛውም የታጠቃ ሀይል በየትኛውም ጫፍ ያለ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጥፋት ሳያጠፋ ከመንግስት ጋር መነጋገር እንደሚችል መግለጹን አስታውቀዋል።

የክልሉን ሙሉ ሰላም ለማምጣት በየደረጃው ያሉ የአማራ ህዝብ፣ ወጣቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሚዲያ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.