Fana: At a Speed of Life!

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አቅም መገንባት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወሳኝ ነው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስለኮሮና ቫይረስ ስለቤት ለቤት ቅኝት እና አሰሳ እንዲሁም ወረርሽኙን ለመከላከል መኖር ያለበትን ቅንጅታዊ አሰራር በተመለከተ አቅማቸውን መገንባት ቫይረሱን ለመከላከል ወሳኝ ተግባር መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ሚኒስትሯ የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተዘጋጀ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚሰጥ ስልጠና ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የተጀመረው ስልጠና ባለሙያዎች አንድ ቦታ መሰብሰብ ሳያስፈልጋቸው በየትኛውም ሠዓት እና ቦታ እንዲከታተሉ ከማስቻሉም በላይ በአንድ ጊዜ በርካታ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ያስችላል ብለዋል።

ስልጠናው በፅሁፍ እና በመልዕክት መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን የመመዘኛ ጥያቄዎችም ተካተውበታል።

በአጠቃላይም ስልጠናው በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚገኙ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በቀበሌ፣ በወረዳ ደረጃ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ፤ በቤት ለቤት የመተንፈሻ አካል ህመም አሰሳ ለማካሄድ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እና ስለቫይረሱ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸውም ያስገነዝባል ነው የተባለው።

በጤና ሚኒስቴር እና በአምረፍ ሄልዝ አፍሪካ ትብብር የተጀመረው ስልጠና በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን ወደፊት ለሌሎች የጤና ጉዳዮች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል መሆኑ ታውቋል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.