Fana: At a Speed of Life!

በሙስና የተጠረጠሩ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጠረጠሩ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ- ኃይሉ አስታወቀ፡፡

ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች የሚነሱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ከመሰረቱ ለመፍታት÷ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ሕገ ወጦችንና ሙሰኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ለረጅም ጊዜ የተቀናጀ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መግለጫ እንዳመላከተው÷ ተገልጋዮች በመደበኛ የመንግሥት ሥርዓት የሚፈልጉትን የፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶችን በአፋጣኝና በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት ሲችሉ ተጠርጣሪዎች የፈጠሯቸው የተንዛዙና እና የተወሳሰቡ አሠራሮች ዜጎችን ለከፋ እንግልት ከመዳረግ ባሻገር ላልተገባ ወጪ ሲዳርጉ ነበር፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ በሙስና ተግባር በመሠማራት የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ እንደነበረ የገለጸው መግለጫው÷ ግለሰቦቹ የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ በወንጀል ተከሰው የጉዞ ሠነዳቸው ለታገደባቸውና ሐሰተኛ የማንነት መገለጫ ላላቸው ሕገ ወጦች ጭምር የፓስፖርት፣ ሊሴፓሴና ቪዛ አየር በአየር በመሸጥ እና በማስተላለፍ፣ መንገደኞች በሌሉበት ጉዞ እንዳላቸው በማስመሰል እና የጉዞ ሠነድ በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደተዘዋወሩ የሚገለፅ ማሕተም በማዘጋጀት ተግባር ተሰማርተው ተገኝተዋል ብሏል፡፡

በተጨማሪም ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ተመልምለው ያለፉ እንደሆኑ በማስመሰል ግለሰቦች ባልተገባ መንገድ ለሥራ ወደ ተለያዩ የዓረብ ሀገራት እንዲወጡ በማድረግ እንዲሁም የሕጋዊ ግለሰብን ፓስፖርት ፎቶግራፍ በመቀየር ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንደተደረሰባቸው የግብረ-ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።

እነዚህ ወንጀለኞች ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የጥቅም ትስስር በመዘርጋት ሙስና ሲፈጽሙ ከመቆየታቸውም ባሻገር÷ ሐሰተኛ የማንነት መታወቂያዎችን በማዘጋጀት ተግባር ላይ ተሰማርተው ከነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደቆዩ ታውቋል ብሏል የጋራ ግብረ- ኃይሉ በመግለጫው።

ይህን ተከትሎም የጋራ ግብረ-ኃይሉ ባደረገው ክትትል÷ ከ200 በላይ የሚሆኑ በሕገ ወጥ መንገድ የተዘጋጁ ፓስፖርቶች እንዲመክኑ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

የወንጀል ድርጊቱም መንግሥትን በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እንዳሳጣው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው ግብረ -ኃይል መግለጫ እንደሚያስረዳው÷ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በወንጀሉ የተሳተፉ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሲያገለግሉ የነበሩ ከከፍተኛ አመራርነት እስከ ባለሙያ ያሉ 42 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በወንጀል ድርጊቱ ተሰማርተው ከተገኙና በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከልም÷ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ግንበቶ አዋልሶን ጨምሮ ዘመድኩን ጌታቸው፣ ከድር ሰዒድ ስሩር፣ አስቻለው እዘዘው፣ አብዱላሂ አሊ መሀመድ (አብዱላሂ ጃርሶ)፣ ቴዎድሮስ ቦጋለ፣ ጌትነት አየለ፣ ጀማል ገዳ፣ ሙላት ደስታ፣ ጅላሎ በድሩ፣ ገነት ኃ/ማርያም፣ ደገፋ ቤኩማ ፣ ወንድይፍራው ሽመልስ ገ/ሰንበት እና ሌሎችም ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡

በተያዙት ተጠርጣሪዎች ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው መግለጫው÷ በግለሰቦቹ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ያላቸው ዜጎች ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ ኦፕሬሽንም የተለያዩ ፓስፖርቶች፣ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎች፣ አየር በአየር የወጡ ሊሴ ፓሴዎችና የታተሙ ቪዛ ካርዶች በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤትና የሥራ ቦታ በተደረገ ብርበራ በማስረጃነት

በእንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር ዙሪያ የሚያካሂደውን ምርመራ፣ ክትትልና ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው የጋራ ግብረ- ኃይሉ÷ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ማኅበረሰቡ ላሳየው የተለመደና ቀና ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.