Fana: At a Speed of Life!

ሌጲስ በዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት የእውቅና ሽልማት አገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር በዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት የእውቅና ሽልማት ማግኘቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘውን የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር በዓለም ድንቅ የቱሪዝም መንደርነት በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡

በአስደናቂ እይታዎች፣ ፏፏቴ፣ አዕዋፋት እና የዱር እንስሳት በውስጡ የያዘው የሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ከቀርከሃ በሚሰሩ የእደ-ጥበብ ውጤቶች በስፋት ይታወቃል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ ስለሺ ግርማ÷ ሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ኢትዮጵያ ለውድድር ካቀረበቻቸው ሰባት የቱሪዝም መንደሮች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንደሩ በአካባቢው ያለው ጥብቅ ደን፣ በርካታ ዕፅዋትና እንስሳቶች፣ ድንቅ ፏፏቴ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ እንዲሁም በተፈጥሮ ጥበቃ ስራ እና በዕደ ጥበብ ስራዎች ጠንካራ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉት መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገውም አንስተዋል፡፡

የቱሪዝም መስሕቦች እንዲለዩ፣ እንዲለሙ፣ በዓለም እንዲተዋወቁ እና በስፍራው ያሉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲመሰረቱ እና ለጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌጲስ ኢኮ ቱሪዝም መንደር ከአርሲ ነገሌ ከተማ በስተምሥራቅ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዓለም ድንቅ መንደርነት የጮቄ ተራራ እና የወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መንደርን ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.