Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ ለጭነት አገልግሎት በ22 የመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ላይ የምህንድስና ማስተካከያ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮቪድ-19 ያሳደረውን ጫና ለመቋቋም አዲስ ስትራቴጂ በመጠቀም ተጨማሪ 22 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ በውስጥ አቅም የምህንድስና ማስተካከያ በማድረግ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

አየር መንገዱ እንዳስታወቀው፥ በአለም ላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ያስቆመው የኮሮና ቫይረስ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪውን ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆም አድርጓል።

በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመንገደኛ በረራዎቹን ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆሙ በመደረጋቸው የአየር መንገዱን ህልውና የሚፈታተንና ከአለም አቀፋዊ ቀውሱ ለመውጣት የስራቴጂክ እቅድ ለውጥ በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ እቃ ጭነት ቢዝነስ በማዞር እየሰራ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። ።

በመላው አለም እየጨመረ ለመጣው የጭነት አገልግሎት ፍላጎት በነበሩት የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖች አጠናክሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

አዲስ የቀየሰውን ስትራቴጂ በመጠቀም የጭነት ማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግ ተጨማሪ 22 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ በውስጥ አቅም የምህንድስና ማስተካከያ ተደርጎባቸው የጭነት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

አየር መንገዱ በመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ውስጥ የሚገኙ መቀመጫዎችን ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ያደረገው አለማቀፍ የአቪየሽንና የቴክኒክ ተቆጣጣሪ አካላት ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች በመከተልና በማሟላት እንደሆነም ገልጿል።

አየር መንገዱ የኮሮናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ህይወት አድን የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን በመላው አፍሪካ በማጓጓዝ ላይ ነው።

የአገልግሎት ተልእኮውን በብቃት ለመወጣትም በመንገደኛ አውሮፕላን የእቃ ማስቀመጫ ቦታ፣ እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ወንበሮች ሳይነሱ ጭነት በመጫን አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የጭነት አገልግሎት ፍላጎት ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን ያመለከቱት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤” የመንገደኛ አውሮፕላኖቻችንን ለጭነትአገልግሎት እንዲውሉ በማጥናትና በማስተካከል የምህንድስና ስራ ላይ የተሳተፉትን የአየር መንገዳችን የአውሮፕላን ጥገና ክፍል /MRO/ ብቁ ባለሙያዎችን ከልብ አደንቃለሁ፣ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ይህ ተግባር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የበርካታ ደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ነው ያሉት።

አገልግሎቱን አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን በማጤን ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ተወልደ፤ አየር መንገዱ በዚህ ፈታኝ ወቅት የዓለምን ማሀበረሰብ ለማገልገል ባደረገው ጥረት ህይወት አድን የሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን በበርካታ መጠንና ፍጥነት አጓጉዟል ብለዋል።

በዚህም አየር መንገዱ አጠቃላይ የአገልግሎት ብቃቱን በማስመስከሩ ምስጋናና አድናቆት እየተቸረው እንደሚገኝም ዋና ሥራ አስፈጻሚው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.