Fana: At a Speed of Life!

እርስ በርስ በመደጋገፍ የቆየ ኢትዮጵያዊ መገለጫችንን ይበልጥ ማጎልበት አለብን – አቶ እንደሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እርስ በርስ በመደጋገፍ የቆየ ኢትዮጵያዊ መገለጫችንን ይበልጥ ማጎልበት አለብን ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ስልጠናቸውን እየወሰዱ የሚገኙት የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ለአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳት በሰበሰቡት ገንዘብ የእድሳት ስራውን አስጀምረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት አቶ እንደሻው ጣሰው÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

እርስ በርስ በመደጋገፍ የቆየ ኢትዮጵያዊ መገለጫችንን ይበልጥ ማጠናከር እና ማጎልበት አለብን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ስራ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ እንዳሻው÷ በክልሉ ስም ለአረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳት እንዲውል የ300 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍስሐ ደሳለኝ በበኩላቸው÷ ብልጽግና ሰው ተኮር ፓርቲ በመሆኑ የህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የፓርቲውም አንገብጋቢ ጥያቄ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ስልጠናቸውን እየወሰዱ የሚገኙት የብልጽግና ፓርቲ ሰልጣኞች ለከተማዋ አቅመ ደካሞች እና አረጋዊያን ቤት እድሳት የሚውል 707 ሺህ 850 ብር ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.