Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የአለም አቀፍ ቅንጅትና ትብብር አስፈላጊ ነው-ዶ/ር ሊያ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት በቪድዮ  ኮንፈረስ  በተጀመረው 73ኛው የዓለም የጤና ጉባኤ ላይ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የአለም አቀፍ ቅንጅት እና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት አመታዊ ጉባኤ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የ194 ሀገራት ተወካዮች በተሳተፉበት ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት ነው።

ጉባዔው በዋናነት አባል ሀገራቱ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ 310 ሺህ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ማተኮሩ ነው የተነገረው።

በዚህም ጉባኤ ላይ በርካታ የሀገሪት መሪዎች ፣ የመንግስት አመራሮች ፣ የጤና ሚኒስትሮች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰም በጉባኤው ላይ ባቀረቡት ንግግር ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየወሰደች ስላለችው እርምጃና በአፍሪካ ውስጥ የነበራትን ሚና አንስተዋል።

ከዚያም ባለፈ የዓለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ነው የገለፁት።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ  ጂንፒንግ ሃገራቸው ቫይረሱን ለመቆጣጠር አበረታች ስራ መስራቷን ጠቅሰው፥ አስፈላጊው ግምገማ ቫይረሱን ከተቆጣጠረን በኋላ ይደረጋል ብለዋል።

አያይዘውም ቻይና ቫይረሱን ለመከላከል የሚውል 2 ቢሊየን ዶላር እንደምትለግስ ቃል ገብተዋል።

በስብሰባው ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት የኦክስፋም አሜሪካ የፖሊሲ እና የመብት ተሟጋች ምክትል ፕሬዝዳንት ፖል ኦበርን÷ “የዘንድሮው ጉባኤው ድርጅቱ ከተመሰረተ በኋላ ምናልባትም በታሪካ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ጉባኤ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።

“ ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አለ ከዚያም ጋር ተያይዞ ግማሽ ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በድህነት ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ” በማለት  ይህ ጉባኤ  ቁልፍ መፍትሄ እንዲያመጣ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ዓለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ነርሶች እና አዋላጆች ያስፈልጓታል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የጤና ባለሙያዎች ድርጅቱ እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.