Fana: At a Speed of Life!

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ገለፃ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገለጻ ተደረገላቸው።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለአምባሳደሮቹ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ዙሪያ ገለፃ ለአምባሳደሮቹ ገለፃ አድርገዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እየተካሄደ ባለው ገለጻ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት እና በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች ተነስተዋል።

በዚህም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት የተደረጉ ውይይቶች ልምን ስኬታማ አልሆኑም የሚለው ላይ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በዋሽንግተን በነበረው ድርድር ላይ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ የነበራቸው ሚና ታዛቢነት ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የአደራዳሪነት ሚናን መያዝ ፈለጉ ለዚህም ስኬታማ አልሆነም ብለዋል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ግልፅነት ለመፍጠር ከፍተኛ አቋም ይዛ ስትሰራ መቆየቷን እና በዚህም በግድቡ ዙሪያ ከ153 በላይ ሰነዶችን ማቅረቧነም አስታውቀዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ በየትኛውም ሀገር ላይ ተጽዕኖ እንደማያደርስም በመግለፅ፤ የተፈጥሮ ሀብትን በትብብር መጠቀም ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያም በዚህ መርህ ነው እየተንቀሳቀሰች ያለችውም ብለዋል።

በአጠቃላይ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም እንደ አህጉር ለአፍሪካ ምን አይነት ጠቀሜታ አለው የሚለው ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዓላማም በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ ውዠንብሮችን እና የተሳሳቱ አስተያየቶችን ለማረም እንዲሁም አፍሪካውያን በጋራ በመሆን አፍሪካዊ መፍትሄ አንዲያበጁ መሆኑንም ተነስቷል።

በገለፃው ላይ የተካፈሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተከተለች ያለው አካሄድ አድንቀዋል።

ግብፅ በግድቡ ዙሪያ እየተከተለች ያለው አካሄድ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ፤ ብቸኛው አማራጭና መፍትሄ ድርድር ብቻ መሆኑንም አስታውቅዋል።

ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሮቹ፥ በህዳሴ ድግብ ዙሪያ አደራዳሪ የሚያስፈልግ ከሆነም የአፍሪካ ሀገራት እና የአፍሪካ ህብረት ይህንን የመወጣት አቅም እንዳላቸውም ገልፀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 73 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ ከፊታችን ሐምሌ ወር ጀምሮ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር መገለፁም ይታወሳል።

በአልአዛር ታደለ

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.