Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ የመከላከያ ሠራዊቱን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እያበረከተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የመከላከያ ሠራዊታችንን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እያበረከተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነዉ ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን 116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በዕለቱም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፥ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች በደርግ ዘመነ መንግሥት የሠራዊቱን ዝግጁነት እንዲያጠናክር ታስቦ ቢመሠረትም በመንግስት ለውጥ ምክንያት የተቋቋመበት አላማ እንዳይሳካ ተደርጓል።
በ2012 ዓ.ም እንደገና ወደ ስራ እንዲመለስ የተደረገው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኢንዱስትሪዎችን ይዞ ቢደራጅም ከትርፋማነቱ ይልቅ ለዘረፋ እና ለብክነት ተጋልጧል ብለዋል።
ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአምራች ስም ቢደራጅም ከ70 ቢሊየን ብር በላይ በመክሰሩ ተቋሙን እና ሃገርን ለውጭ ዕዳ መዳረጉንም ነው የተናገሩት።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ ወደ ሲቪል ተቋም ቢቀየርም መከላከያን በኢንዱስትሪ ለማጠናከር በአዲስ አደረጃጀት ወደ ስራ እንዲመለስ በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአዲስ አደረጃጀት የተቋቋመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ከተመሰረተበት 2012 ዓ.ም ጀምሮ የቅርብ ክትትል በማድረግ ኢንዱስትሪዎች መሠረታዊ ለውጥ እንዲኖራቸው እና ትርፋማ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ተችሏል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በአዲስ አመራር አደራጅተን ወደ ምርት እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ወደ ትርፋማነት ተሸጋግሯል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ በጥናት እና ምርምር አስደግፎ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም በበኩላቸው ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን የአጭር ፣ የመካከለኛ እና የረጅም ዕቅዶችን አውጥተን ወደ ስራ ስንገባ ከ25 በላይ መመሪያና የተለያዩ አሰራሮችን አዘጋጅተን ነው ብለዋል።
ዋነኛ ትኩረቱም መገጣጠም እና ማደስ አይደለም ያሉት አቶ ጌታቸው ኃይለማርያም አዳዲስ ማሽኖችን እና ፋብሪካዎችን በማስፋፋት በትጥቅ አቅም ራስን መቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.