Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶች መወገዳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶች መወገዳቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ የጤና፣ የንግድ፣ የፍትሕ፣ የግብርና፣ የትምህርት ቢሮዎችና የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ ከ17 ተቋማት ጋር በምግብና ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር የሚያስችል የትስስር ሰነድ ተፈራርሟል።

ባለስልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ በምግብና ጤና ነክ ጉዳዮች ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉእመቤት ታደሰ በወቅቱ እንደገለጹት÷ ባዕድ ነገር በተቀላቀለባቸው ምግቦችና የመጠቀሚያ ጊዜ ባለፈባቸው መድኃኒቶች አማካኝነት የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመቀነስ እየተሰራ ነው።

ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድኃኒቶች ተወግደዋል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጉድለት በተገኘባቸው 18 ድርጅቶችና ጤና ተቋማት ላይ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ብቃት ማረጋገጫ ስረዛ እርምጃ መወሰዱን ዋና ስራአስኪያጇ አመልክተዋል።

ጉድለት በተገኘባቸው 31 የመድኃኒት ችርቻሮ ንግድ ላይ በተሰማሩ ድርጅቶችና በምግብ ማምረቻ፣ ማከፋፈያ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ በተደረገው ቁጥጥርም ጉድለት በተገኘባቸው 734 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።

ግምታቸው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ወደ ሕብረተሰቡ ቢሠራጩ የጤና ዕክል የሚፈጥሩ ምግቦች፣ መጠጦችና የምግብ ማብሰያ፣ ማቅረቢያና ማሸጊያ መሳሪያዎች መወገዳቸውንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 235 ኪሎ ግራም መድኃኒቶችና ሌሎችም መወገዳቸውን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.