Fana: At a Speed of Life!

ከ 800 ግራም በላይ ወርቅ ሲከፋፈሉ የተገኙ 3 ግለሰቦች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 11 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ800 ግራም በላይ ወርቅ በተሸከርካሪ ውስጥ ሆነው እየመዘኑ ሲከፋፈሉ የተገኙ 3 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ መጀመሩን ፖሊስ አስታወቀ።
 
ግለሰቦቹ ቀደም ሲል በአንድ የወርቅ መሸጫ ሱቅ ላይ የስርቆት ወንጀል ስለመፈፀማቸው ማስረጃ መገኘቱንም የሳሪስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል።
 
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ዳማ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የወርቅ መሸጫ ሱቅ ላይ 60 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የጣት ቀለበቶች ገዢ መስለው በገቡ ግለሰቦች መሰረቃቸው ተገልጿል።
 
በዚህም ፖሊስ የፈፃሚዎቹን ማንነት በማወቅ ለመያዝ ክትትል እያደረገ ባለበት ሁኔታ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ/ም በክፍለ ከተማው ወረዳ 9 ቶታል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሶስቱ ግለሰቦች በተሽከርካሪ ውስጥ ሆነው ባለ 14፣ ባለ 18፣ እና ባለ 21፣ ካራት በአጠቃላይ 886 ግራም ወርቅ ይዘው እየመዘኑ ሲከፋፈሉ በክትትል ፖሊስ አባላት በጥርጣሬ መያዛቸው ነው የተነገረው።
 
ከዚም ባለፈ አንደኛው ግለሰብ እጅ ላይ በወቅቱ 80 ሺህ ብር እንደተገኘ ምክትል ኢንስፔክተር አበራ አስረድተዋል።
 
በወቅቱ ሳሪስ ዳማ ሆቴል አካባቢ የስርቆት ወንጀል በተፈፀመበት የወርቅ መሸጫ ሱቅ ውስጥ የተገጠመው የደህንነት ካሜራ የፈፃሚዎቹን ማንነት ቀርፆ እንደነበረም ጠቁመው÷በካሜራው ወንጀሉን ሲፈጽሙ የታየው ምስል ውስጥ ወርቁን ሲከፋፈሉ ከተያዙት የሶስቱ ግለሰቦች ምስል መገኘቱን ተናግረዋል ።
 
ከዚያም ባለፈ የግል ተበዳዮችም ከሌሎች ተጠርጣሪዎች መሃል በምስሉ ላይ ያሉትን ሶስቱን ግለሰቦች መርጠው መለየታቸውን ገለፀዋል።
 
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው ያሉት መርማሪው፥ ገዢ መስለው የሚመጡ ሁሉ ገዢ ስላልሆኑ በተለይም የወርቅ ጌጣ ጌጦች በቀላሉ ሊያዙና ሊደበቁ የሚችሉ በመሆኑ በጌጣ ጌጥ መሸጫ ሱቆች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችና ነጋዴዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.