Fana: At a Speed of Life!

ከባንኮች የሚወጣን ጥሬ ገንዘብ የሚገድብ መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከባንኮች የሚወጣን ጥሬ ገንዘብ የሚገድብ መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ መመሪያው የገንዘብ ዝውውርን ወደ ስርአት በማስገባት ወንጀልንና የግብር ስወራን ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል ብለዋል።

ዛሬ የሚተገበረው አዲሱ መመሪያ ለግለሰብ በቀን እስከ 200 ሺህ እና በወር ደግሞ እስከ 1 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ሲፈቅድ ለኩባንያዎች ደግሞ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር እና በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድረስ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ይችላሉ ተብሏል።

ወጪ የጥሬ ገንዘብ ገደቡ መጠን ላይ ምንም ለውጥ ሳያሳድር ከተገደበው የጥሬ ገንዘብ በላይ ለሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከአካውንት ወደ አካውንት ወይንም በቼክ ወይንም ደግሞ በሲፒኦ ተጨማሪ ክፍያን መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።

መመሪያው በልዩ ሁኔታ መታየት ያለባቸው ከፍያዎችን በተመለከተም የራሱ ሂደት ያለው ሲሆን፥ የልዩ ሁኔታ ክፍያ ለየባንኮች ፕሬዚዳንቶች ስልጣን እንደሰጠና ውሳኔ አሳልፈው ክፍያው የተፈፀመ እንደሆነም በየሳምንቱ ለብሄራዊ ባንክ በሚያደርጉት ሪፖርትና ክትትል እንደሚያልፍም ተነግሯል።

መመሪያውን ጥሶ የተገኘ ባንክም ከፈጸመው ክፍያ የ25 በመቶ ጥብቅ ቅጣት እንደሚፈጸምበትም ተነግሯል።

መመሪያው በሁሉም ባንኮችና አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት ላይ እንደሚተገበርም ታውቋል።

መመሪያውን ለመፈጸም ክሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ስምምነት መደረሱም ታውቋል።

በተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.