Fana: At a Speed of Life!

ፍቼ ጫምባላላ ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር የሲዳማ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እሴቶች መገለጫ ነው-ዶ/ር ሂሩት ካሳው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢ.ፌ.ድ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ለሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ  ፍቼ ጫምባላላ በዓል  ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት  በዓሉ ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር የሲዳማ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እሴቶች መገለጫ መሆኑን ገለጹ።

ሚኒስትሯ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጨምበላላ ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ከነሙሉ ክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ደማቅና የኩራታችን ምንጭ የሆነ ባህላዊ ዕሴታችን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዛሬ ላይ በዓሉ የሲዳማ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ከዚያም አልፎ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሃብት ሆኖ ይገኛል ነው ያሉት።

ለዚህም ለቀደምት አባትና እናቶቻችን ክብር ይግባቸውና ይህንን የመሰለና ለአገራችን እንደ ውብ ፈርጥ አምረውና ጎልተው ከሚታዩ በዓላት አንዱ የሆነውን ይህንን ባህላዊ ዕሴት ለዚህ ትውልድ እንዲደርስ አድርገዋል።

ይህ በዓል ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር የሲዳማ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔሃታዊ እሴቶች መገለጫም መሆኑን ጠቁመው÷ ባህላዊ ሁነቱ በዋናነት ሰላምን፣ መከባበርን፣ አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ልማትን፣ እርቅን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብር ትልቅ ሀብት ነውም ነው ያሉት።

ፊቼ ጫምባላላ ስለ ሠላም የሚሠጠው ከፍ ያለ ቦታም በሠው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ስጦታዎችም ጭምር የሠላም አየር እንዲነፍስ የሚያደርጉ እሴቶች በውስጡ አጭቆ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ አብሮ በመኖር ሂደት መጋጨት እንደ ምድር የስበት ሕግ የማይቀር መሆኑን በጥልቀት በመረዳት ህፃናትና ሴቶች ዓለም አሁን ከተኛበት ተነስቶ የእኩልነት መብትና የፆታ ጉዳይ እያለ ከመስበኩ አስቀድሞ ሲዳማ በፊቼ ጫምባላላ አክብሮቱን ሲያሳይ ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ነው ብለዋል።

ፍቼ ጨምበላላ የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት በመሆን ከህፃን አስከ ሽማግሌ በፍፁም ደስታ የሚከበረው ይህ ታላቅ በዓል ከነሙሉ ክብሩና ለዛው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ መሸጋገር ይኖርበታል ስለሆነም  አሁን ያለው ትውልድ አደራም ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ሂሩት አያይዘውም ለዚህም ባህላዊ ዕሴቱ በውስጡ አቅፎ የያዛቸውን መሰል ጠቃሚ ትሩፋቶችን ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ በጽሁፍ፣ በምስል እንዲሁም በምስልና ድምፅ ከትቦ መያዝና ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር በሚያስችል መልኩ ሰንዶ ማስቀመጥ የዘርፉ ምሁራንና የአካባቢው ማህበረሰብ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ይህንን ማድረግ ከተቻለ የሲዳማ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ በመኖርና በሥራ ያዳበራቸውን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ክንዋኔዎችንና አስተሳሰቦችን ጠብቆ ማቆየት ይቻላል  ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

አያይዘውም ከዚህ ባሻገር ሁነቱ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ከማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ዓለም በቅርሶች መካከል አንዱ እንዲሆን በማድረግ የመዘገበው በመሆኑ በዓለም ህዝቦች ዘንድ እየታወቀ  እንደሚገኝ ጠቁመው÷ይህን መልካም ዕድል በዓሉን ይበልጥ በማጎልበትና ሳቢ በማድረግ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው ብሎም ወደ አገራችን እንዲመጡ በሂደቱም ባህላዊ ሁነቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ማህበራዊና ምጣኔሃብታዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ ለማድረግ አቅዶ መሥራትን እንደሚጠይቅም  ተናግረዋል ፡፡

ለዚህም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ሁላችሁም እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም ፊቼ ጫምባላላ በተለያዩ ሥነሥርዓቶች ታጅቦ ያለማቋረጥ ለረጅም ዘመናት በድምቀት ሲከበር የቆየ ሲሆን÷ የዘንድሮ ፊቼም ከግንቦት 12 እስከ 13/2012 ዓ.ም የሚውል ቢሆንም ያለንበት ወቅት አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ብሎም በሀገራችን በተከሰተበት ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በ”ጉዱማሌ” ወይም በባህላዊ አደባባይ፣ በቄጣላና በተለያዩ ውብ ባህላዊ ክንዋኔዎች እንደማይከበር ገልጸዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግም ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች በዓሉን በየቤታቸው እንዲያከብሩ የሲዳማ አባቶች ባህሉ በሚፈቅደው መሠረት ውሳኔ እንዳስተላለፉ ተረድተናል።

ይህም የአባቶቻችንን ብልህነት፣ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት በግልፅ ያሳየ በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን ያሉት ሚኒስትሯ።

አያይዘውም  ያለንበት ወቅት ከመቸውም ጊዜ በላይ መተባበርንና መደጋገፍን የሚጠይቅ በመሆኑ  ፍቼ ጨምበላላ የፍቅርና የመተሳሰብ ተምሳሌት እንደመሆኑ በዚህ ወቅት ኮቪድ 19 ባስከተለው ጫኛ የተነሳ ኑሯቸው የተናጋባቸውን ወገኖች በያሉበት አለንላችሁ በማለትና የሚፈልጉትን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ከጎናቸው ልንቆምና ልንታደጋቸው ይገባል ብለዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግስት የህዳሴውን ግድባችንን ጨምሮ ሌሎች ልማታዊ እቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለሚያደርገው ጥረት የየበኩላችሁን ድርሻ በማበርከት የአገራችንን ከፍታ ዕውን ለማድረግ እንድትተጉ በታላቅ አክብሮትና ትህትና አደራ ለማለት እፈልጋለሁ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ።

ጫምበላላ ከአንዱ ዘመን ወደሌላው መሻገርን የምናበስርበት እንደሆነ ሁሉ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ልብ ለልብ ተሳስረን አገራችንን ከዚህ ፈታኝ ዘመን ለማሻገር ቆርጠን እንነሳ ለዚህም ፈጣሪችን ይርዳን  በማለት እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.