Fana: At a Speed of Life!

በአልጄሪያ በሀሰተኛ መረጃ አንድን ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ 38 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአልጄሪያ ፍርድ ቤት አንድን ግለሰብ “ሰደድ እሳት አስጀምሯል” በሚል የተሳሳተ መረጃ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ 38 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ወሰነ፡፡

በአልጄሪያ ካብይሊ ተብሎ በሚጠራ ግዛት አካባቢ በፈረንጆቹ 2021 ነሐሴ ወር ላይ ከፍተኛ የሰደድ እሳት ተቀስቅሶ ነበር፡፡

በዕለቱም የአካባቢው ነዋሪዎች የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲረባረቡ ይታያሉ፡፡

ይህንን የተመለከተው ድጃሜል ቤን እስማኤል የተባለው ግለሰብም እሳቱን ለማጥፋት የሚታገሉ ሰዎችን ለማገዝ ወደ ስፍራው ያቀናል፡፡

ይሁን እንጂ በቀናነት ሰዎችን ለማገዝ ወደ ቦታው ያቀናው የ38 ዓመቱ ግለሰብ ፍጹም ያልጠበቀው ድርጊት ገጥሞት ህይወቱን ተነጥቋል።

እሳቱን በማጥፋት ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ድጃሜል ቤን እስማኤልን ሰደድ እሳቱን አስነስቷል በሚል ሀሰተኛ መረጃ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቡን በደቦ ፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ ከመደብደብ ባለፈ ወደ ሰደድ እሳቱ በመጨመር ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የአልጄሪያ ፍድር ቤት ትናንት በዋለው ችሎትም ግለሰቡን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የተጠረጠሩ ሰዎችን ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከልም 38 ግለሰቦች በሞት ፍርድ እንዲቀጡ ነው ፍድር ቤቱ የወሰነው፡፡

በተጨማሪም በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሌሎች 29 ተከሳሾች ከ3 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስር እንዲቀጡ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.