Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከ2 ሺህ 700 በላይ በጎዳና ላይ የሚኖሩ አረጋዊያንን የማንሳት ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከተለያዩ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከላት ጋር በመተባበር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 2 ሺህ 754 አረጋዊያንን የማንሳት ስራ ጀመረ።

በዛሬው ዕለትም ከ286 በላይ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ አረጋዊያንን ወደ ክብረ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል የማንሳት ስራ መጀመሩን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተክሌ ደሬሳ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናትም ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ለተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አረጋዊያንን በሜቅዶኒያ እና በመቅድም ኢትዮጵያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከላት ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አቶ ተክሌ አስታውቀዋል።

ቢሮው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ ማዕከላቱ ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊው ምርመራ እንደተደረገላቸው ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።

የክብረ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ሙንኤ ማዕከሉ ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ አረጋዊያንን ከጎዳና በማንሳት እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት የከተማ አስተዳደሩ በሰጣቸው 10 ሺህ ካሬሜትር ቦታ ላይ በዛሬ ዕለት ያልገቡትን ሳይጨምር ከ200 በላይ አረጋዊያንን በመንከባከብ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሬተሪ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.