Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በመቐለ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው የሃይል ድርጊት መወገዝ እንዳለበት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመቐለ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የተሰባሰቡ ወጣቶችን በፖሊስ ለመበተን በተደረገ ጥረት የተፈጠረ አለመግባባት ለአንድ ወጣት ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሰሜን ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሓዱሽ ሕዱግ ለኢዜአ እንደገለጹት ግጭቱ የተፈጠረው ባሳለፍነው እሁድ በአንድ ሥፍራ የተሰባሰቡ 10 የሚሆኑ ወጣቶችን ፖሊስ ለመበተን በሞከረበት ወቅት ነው።

ወጣቶቹ የተጠየቁትን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተፈጠረው አለመግባባት ለ1 ወጣት ሕይወት መጥፋትና ለሌሎች ሁለት ወጣቶች መቁሰል ምክንያት መሆኑን ተናግረው በግጭቱ የቆሰሉት ወጣቶች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎም የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ድርጊቱን ያወገዘ ሲሆን፥ በፀጥታ ሀይሎች በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ባለፈው ትግራዋይ ወጣት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ፤ ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለአብሮ አደግ ጓደኞቹ እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ መፅናናትን ተመኝቷል።

ህዝቡ በዚህ ፈታኝ ወቅት ያጋጠመውን ድርብ ፈተናና ችግር በማለፍ ወደሚፈልገውና ወደሚገባው የሰላም፣ የብልጽግና የመረጋጋት፣ የዲሞክራሲና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት ሆነ በፓርቲ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች ህዝባዊነታቸው፣ የአመራር እሴቶቻቸውና ጥበባቸው የሚፈተንበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንደሚገኝም ማስተዋልና መበርታት ይገባል።

የትግራይ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድነት በመሆን ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በከፈለው መስዋእትነት የሰላምና ዴሞክራሲ ብልጭታ የማየት ፍላጎቱ በቀረበው ቁጥር የሚሸሽበት ምናባዊ አለም ብቻ እየሆነበት መጥቷል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

በቅርቡ የአንድ ወጣት ህይወት እንዲያልፍ ከመደረጉም በሻገር ከሁለት ቀናት በፊት በመቐለ ከተማ የተከሰተው ለአንድ ወጣት ክቡር ህይወት ህልፈትና ለሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ በክልሉ ውስጥ የሰላምና ዲሞክራሲ እጦት ማሳያ ነው ሲልም ገልጿል።

ሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ በሆነው የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሪር የሀዘንና ውጥረት ድባብ ውስጥ ይገኛል ያለው ፓርቲው፥ ይህ ክቡር የሰው ህይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በህግ አግባብ ለማስጠበቅ ሃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈፀመ መሆኑ እጅጉን በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል፤ይህም ድርጊት ብዙ መስዋእት ለከፈለ ህዝብ የማይገባው ነው ብሏል።

ራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ህይወታቸውን እስከመቅጠፍ የደረሰ የሃይል እርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር ነው ያለው የትግራት ብልፅግና ፓርቲ፥ ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው የእርምት እርምጃ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.