Fana: At a Speed of Life!

ሠራዊቱ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ሁሉ የህዝቡ ጠንካራ ደጀንነት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው – ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሠራዊቱ ሀገርን ለማጽናት በሚያደርገው እንቅሰቃሴ ሁሉ የህዝቡ ደጀንነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ ገለጹ።

116ኛው የሠራዊት ቀንን በማስመልከት የዕዙ አመራሮችና አባላት ከሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ የፓናል ውይይት አድርገዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋ፤ ሠራዊቱ ሀገሩን ለማጽናት ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈለ መምጣቱን አስታውሰዋል።

ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተንቀሳቀሰባቸው ቦታዎች ሁሉ የህዝቡ ጠንካራ ደጀንነት ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም አንስተዋል።

ህዝባችን የጀርባ አጥንታችን ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን፤ ህዝቡ ሠራዊቱ ኃይል በፈለገ ጊዜ ሳይሰስት ልጁን መርቆ የሚሰጥ ደጀን መሆኑን ተናግረዋል።

ሠራዊቱም የለውጡ አካልና በሪፎርም ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገርና ህዝብ የጣለበትን ትልቅ አደራ በብቃት ለመወጣት የሰላም ሃይል ሆኖ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ጽንፈኞች ሀገር ለመበታተን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቱ ትውልድ ይህንን ተገንዝቦ ሀገር ለማጽናት ሊታገላቸው እንደሚገባ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን አስገንዝበዋል።

የህብረተሰቡን ሰላም ለማወክና ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ሀይሎችን መታገልና መከላከል እንደሚገባም ገልፀዋል።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አዳነ ተክለጊዮርጊስ በበኩላቸው ”መከላከያ ሠራዊት ሀገር ታፍራና ተከብራ እንድትኖር እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ክብር መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የጽንፈኞች ሴራን ለማምከን በሚደረገው እንቅሰቃሴ ሁሉ የከተማው አስተዳደር አመራር አባላትና የጸጥታ አካላት ከሠራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሠራዊቱን ለማጠናከር በሚደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅሰቃሴ ሁሉም ድጋፍና ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ሥራዎች መከናወን የሚችሉት ሰላም ሲሰፍን ነው በማለት ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.