Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር በኮምቦልቻ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ክልል ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር አብዱ ሁሴን በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በመገኘት የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ ከ128 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን የኮምቦልቻ ሁለገብ መናኸሪያ መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በ17 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነባውን የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሼድ ፣ የተጀመሩ የትምህርት ቤት ግንባታ ሂደቶችን እንዲሁም ሌሎች የልማት ሥራዎችን መመልከታቸውም ተጠቁሟል፡፡

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የተጀመሩት የልማት ፕሮጀክቶች በተገቢው ጥራት እና ጊዜ ተጠናቀው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በከተማ አሥተዳደሩ በኩል እየተደረገ ያለዉን ጥረት አድንቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግም መግለፃቸውን የኮምቦልቻ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ አብዱ አክለውም የሕዝብን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነት እና በተቀናጀ መልኩ ለመመለስ ከምንም በላይ ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሰላሙ ዘብ እና ባለቤት እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.