Fana: At a Speed of Life!

ከ160 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ160 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ልብሶች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የቤት ዕቃዎች፣ ብረታ ብረቶች፣ ምንጣፎች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ጫማዎች፣ መድሃኒቶች፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች፣ ሽቶዎች፣ ደብተሮች፣ የዝናብ መከላከያ ሸራዎችና ሚስማሮች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች፣ መነጽሮች፣ ጌጣጌጦችና የተለያዩ የውበት መጠበቂያ ክሬሞችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች መነሻቸውን ሱማሌ ላንድ በማድረግ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በመግባት ላይ ሳሉ በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት ልዩ ስሙ አርሙ ካሴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፌደራል ፖሊስ የምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላትና በጉሙሩክ ሰራተኞች የተቀናጀ ሥራ ተይዘዋል ተብሏል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ-3 ኢት. 71945፣ ኮድ-3 ኢት. 14071፣ ኮድ-3 ኢት. 74192 እና ኮድ-3 ኢት. 74632 በሆኑ አራት ተሽከርካሪዎች ላይ እንደተገኙም ተገልጿል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ 160 ሚሊየን 523 ሺህ 671 ብር የሚገመቱ ሲሆን በጉሙሩክ ኮሚሽን ድሬዳዋ ቅርጫፍ ገቢ ተደርጎ ምርመራ እየካሄደ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.