Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት ናት – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት መሆኗን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፤

በዛሬው ዕለት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሀገርአቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ዕለቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ መልክ ተላብሶ በሚኒስቴር ደረጃ የተመሰረተበት ቀን ነው፡፡

ኢትዮጵያ 116 ዓመታትን ያስቆጠረ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ፀንቶ የቆየና ሀገርን ያፀና የመከላከያ ተቋም ባለቤት መሆኗ ዛሬ ላይ ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትልማችን እንደ ወረት የሚወሰድ በጎ የታሪካችን አካል በመሆኑ እለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይዘከራል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተመሠረተበት ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ጀምሮ የአያት ቅድመ አያቶችን ወኔ፣ የሀገር ፍቅርና ጀግንነት ተላብሶ በፅናት ቀጥሏል፡፡ በደም መስዋዕትነት በተጻፈው አኩሪ ታሪኩ ሀገርን እየታደገ ዛሬ ላይ የደረሰው መከላከያ ሠራዊታችን፥ ምንግዜም ቢኾን ቃልኪዳኑ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን አንድ ክፍለ ዘመን በተሻገረ ታሪኩ ሀገር አፅንቷል፣ ሉዓላዊነታችንን አስከብሯል፣ የግዛት አንድነታችንን አስጠብቋል፣ በደምና አጥንቱ ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ አሸጋግሯል፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን በዘመናት መካከል ኢትዮጵያ ላይ የሚደቀኑ ፈተናዎችን በፅናትና በጀግንነት እየተሻገረ የሚያሸንፍ ድል አብሳሪ ሠራዊት ሆኖ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና ሳያገኙና ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቁ በወቅቱ እጅግ የተደራጀውን የወራሪ ኃይል በአድዋ ድል አድርገው ለቀጣይ ትውልድ ነፃ ሀገርን አስረክበዋል፡፡

በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ራሳቸውን “ጥቁር አንበሳ” በሚል ስያሜ አደራጅተው ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ ሲዋደቁ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ሀገራቸውን ለድል አብቅተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊታችን በካራማራ ተራራ ወራሪውን ኃይል በመምታት ዳር ድንበራችንን አስከብሯል፡፡

ከውስጥም ሆነ ከውጭ የኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑ ኃይሎችን በሙሉ በተለያዩ ጊዜያት በጥንካሬ በመዋጋት ክቡር መስዋዕትነት የከፈለውም ይኸው ለዘመናት ሲገነባ የመጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡

ከሀገር ውስጥ አልፎ ዝናው በዓለም የናኘው መከላከያ ሠራዊታችን፣ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በርዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በሌሎችም ሀገራት የሰላም ማስከበር ግዳጆቹን በብቃት በመወጣት የጀግነታችን ምልክትና የኩራታችን ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በመሆኑም ከጥንት እስከ ዛሬ የሉዓላዊነታችን ዋስትና፣ የኩራታችን ምንጭ፣ የፈተና ጊዜ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በሃገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን ማክበር ነው፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ በየቦታው ከሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመፋለም ሀገሩን እያፀና፣ የሕዝብንም ሰላም እያስጠበቀ የሉዓላዊነት ዋስትና፣ የክፉ ቀን ምሽጋችን ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ ከዛሬ አሻግረው ነገን የማያስቡ ፅንፈኞች የጀግናውን መከላከያ ሠራዊታችን ስም በሀሰት ለማጠልሸት ዘወትር ያለ እረፍት ቢተጉም ሰራዊታችን ለእናት ሀገሩ የገባውን ቃልኪዳን በልቡ አኑሮ በዚህች ሰዓትና ደቂቃ ሳይቀር በየጦር ሜዳው ለሃገሩ ተጋድሎ እያደረገ ነው፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመፋለም፣ ዳር ድንበርን በማስከበር በሰማይም ኾነ በምድር ኢትዮጵያችንን ቀን ለሊት ፈተናዋን እያሻገረ ሞቷንም እየሞተላት ነው፡፡

በመሆኑም ኹሉም ኢትዮጵያዊ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚከፍሉትን ታላቅ መስዋዕትነት በመገንዘብ የተለመደውን ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በየተሰማራንበት የሥራ ገበታ እንደ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሁሉ በወኔ፣ በትጋትና በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት ልንሠራ ይገባል፡፡

በተፈተነ ጊዜ ኹሉ የሚፀና የድል ሠራዊት!

ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.