Fana: At a Speed of Life!

50 የእጅ ቦምቦችን ለሸኔ ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች በፍ/ቤት የተፈቀደላቸው ዋስትና ተሻረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 50 የእጅ ቦምቦችን ለሸኔ ሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች በእስር ፍርድ ቤት የተፈቀደላቸው ዋስትና ተሻረ፡፡

ለተከሳሾች የተፈቀደላቸውን ዋስትና የሻረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ሲሆን÷ተከሳሾችም 1ኛ አማኑኤል ግርማ፣2ኛ አብዶ መላኩ እና 3ኛ ደጋጋ ፈቀደ ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ና ለ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9/ሐ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ነው ክስ ያቀረበባቸው።

ተከሳሾቹ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በውሳኔ ቁጥር 10/2013 ሽብርተኛ ብሎ የተሰየመውን ሸኔ በቀጥታ እየረዱ መሆኑን እያወቁ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሶችንና ተተኳሽ ጥይት በማቅረብ እና ድጋፍ ማድረግ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጠቅሷል።

በተለይም 1ኛ ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀስ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል ከሆነው ነጋሳ ምሬሳ በትግል ስሙ አዱኛ ተስፋዬ ከተባለ ሰው ጋር በመገናኘት በነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ አባል እና ስሙ ካሳሁን በሚባል ግለሰብ አማካይነት ከአፋር ክልል አዋሽ ከተማ ቦምብ ይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ እና ተቀብሎ ”እኔ በምልከው ሌላ ሰው ትልክልኛለህ ” በማለት እንደተነገረው ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

ይኸው 1ኛ ተከሰሽም በጉዳዩ በመስማማት ጓደኛው ለሆነው ለ2ኛ ተከሰሽ ጉዳዩን በማሳወቅና ቦምቡን አብረው ሄደው ተቀብው ለማምጣት በመስማማት በነጋታው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ጋርመንት ወደሚባል ቦታ በመሄድ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ 50 ኤፍ ዋን የእጅ ቦምብ ከ8 የቦምብ ፊውዝ ጋር ማንነቱ ለጊዜው ካልተለየ ግልሰብ በመረከብ ወደ 2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት በመውሰድ ደብቀው ማስቀመጣቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ባለቤቱና እናቱ ወደ ቤት እየመጡ መሆኑን እና ”ቦምቡን አውጥተን ሌላ ቦታ ማስወቀመጥ አለብን ” በማለት ለ1ኛ ተከሳሽ ከገለጸ በኋላ 1ኛ ተከሳሽም ሃሳቡን በመቀበል ጉዳዩን ጓደኛው ለሆነ ለ 3ኛ ተከሳሽ በማሳወቅ 3ቱም ተከሳሾች በሃሳቡ ተስማምተው ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ወደ 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመውሰድ አንድ ላይ በጋራ በመሆን ወደ 2ኛ ተከሳሽ ቤት መሄዳቸው በክሱ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ ቤት አውጥተው 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመደበቅና ለሸኔ ሽብር ብድን አባል ለሆነ ግለሰብ ለማቀበል በማሰብ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ በተደረገባቸው ክትትል ቀን 9፡00 ሰዓት አካባቢ 3ቱም ተከሳሾች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ሰፈራ ተብሎ የሚጣራ አካባቢ በሚገኝ የ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ከ50 ኤፍ ዋን የእጅ ቦምብ እና ከ8 የቦንብ ፊውዞች ጋር እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ÷ የሽብርተኛ ድርጅት የመርዳት ሙከራ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ዐቃቤ ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ያቀረበና ክሱም ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ የዋስትና መብት ይፈቀድልን ጥያቄ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3 ኛ የሕገመንግስትና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ተረኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር።

ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹ የሽብር ቡድኑ አባል መሆናቸውን ጠቅሶ በዋስ ቢወጡ በተመሳሳይ የሽብር ተግባር ላይ ሊሰማሩና የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄን በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍርድ ቤቱም የተከሳሾች የዋስትና ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው ሊገደብ አይችልም በማለት የዐቃቤ ሕግ ክርክርን ውድቅ በማድረግ በአንድ ዳኛ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ የስር ፍርድ ቤቱ የፈቀደውን ዋስትና በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ጠይቋል።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የዐቃቤ ሕግን የይግባኝ አቤቱታ መርምሮ ያስቀርባል በማለት የስር ፍ/ቤት ለተከሳሾቹ የፈቀደውን ዋስትና መብት አግዶታል።

ከዚህ በኋላም ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ አቤቱታ ላይ በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደላቸው ዋስትና ተገቢ ነው በማለት እንዲፀናላቸው ጠይቀው በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ላይ መልስ ሰጥተው ነበር።

ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹ በእስር ፍርድ ቤት የተሰጣቸው የዋስትና መብት አግባብ እንዳልሆነ እና የዋስትና መብታቸው በሁኔታዎች ሊገደብ የሚችልበትን የሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀመጣቸውን ድንጋጌዎች ጠቅሶ የመልስ መልስ አቅርቧል።

አጠቃላይ የግራ ቀኝ ክርክር እና የመልስ መልሱን የመረመረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ፈጽመውታል ከተባለው የወንጀል ሙከራ ተግባር እና ከሁኔታዎች እንዲምሁም ዋስትና መብት ሊገደብ ከሚችልባቸው ድንጋጌዎች አንጻር መርምሮ የእስር ፍርድቤቱ የፈቀደው ዋስትና ተገቢነት የለውም በማለት ፍ/ ቤቱ የሰጠውን ዋስትና ሽሮታል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.