Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ አፍሪካውያን ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የማይልኩ ከሆነ ለእስር የሚዳርግ ህግ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ካልገቡ ማረሚያ ቤት ሊወርዱ የሚችሉበትን ትልቅ የትምህርት ህግ አጽድቋል።

የትምህርት ህጉ ማሻሻያ በፈረንጆቹ 1994 በሀገሪቱ የአፓርታይድ ስርዓት ካበቃ በኋላ ትልቁ ተብሎለታል።

በመሠረታዊ የትምህርት ሕጎች ማሻሻያ (ቤላ) መሠረት ልጆቻቸው ከዘገዩ ወይም ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ካልተመዘገቡ እስከ 12 ወራት ለሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊዳረጉ ይችላሉ ነው የተባለው።

ማሻሻያው በሁሉም ትምህርት ቤቶች አካላዊ ቅጣትን እንደሚከለክልም ተመላክቷል።

ገዥው ፓርቲ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ህጉ “ታሪካዊ እና ወቅታዊ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚያስችል የትምህርት ስርዓትን ይለውጣል” ብሏል።

ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ ዲሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) ማሻሻያው ትምህርት ቤቶች በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ እና ለትምህርት ውድቀት እንደሚዳርግ በመግለጽ ውሳኔውን አውግዞታል።

ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት ተቃውሞ ያነሳው ፓርቲው ይህ ህግ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መንግስትን ወደ ህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት እንደሚወስድም ዝቷል።

በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫ ያለው (ኤኤንሲ) ፓርቲ በድምጽ ብልጫ እንዲጸድቅ ያደረገ ሲሆን በ223 ድጋፍና በ83 ተቃውሞ በትናንትናው ዕለት ማሻሻያው ህግ ሆኖ ጸድቋል።

የትምህርት ባለሙያዋ ሜሪ ሜትካልፍ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በማይልኩ ወላጆች ላይ ቅጣት ሊጣል ይገባል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ ከ10 ተማሪዎች 8ቱ በ10 ዓመታቸው ለንባብ እንደሚቸገሩ አንድ ጥናት ማረጋገጡን ዘገባው አክሎ ገልጿል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.