Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየው የኮቪድ-19 ስርጭት በሁለቱ ወራት ውስጥ ከነበረው ይበልጥ አሳሳቢ ነው -የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየው የኮቪድ-19 ስርጭት በሁለቱ ወራት ውስጥ ከነበረው ይበልጥ አሳሳቢ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

እንደ ሃገርና እንደ አዲስ አበባ ከተማ ባለው የቫይረሱ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩትና የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የየዕለት ቁጥሩ ቢለያይም ባለፉት 2 ሳምንታት ውስጥ ብቻ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ተነጥሎ ሲታይ 230 መሆኑ የቫይረሱን የስርጭት ሁኔታ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።

ይበልጡንም ደግሞ ባለፉት 2 ቀናት ቫይረሱ በ49 ሰዎች ላይ መገኘቱን እንደ አብነት በማንሳት የቫይረሱ ስርጭት መጠናከር ከህብረተሰቡ የጥንቃቄ ጉድለትና መዘናጋት የመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው፥ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው 365 ሰዎች 56ቱ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽታው ተጠቂ ግለሰብ ጋር ንክኪ ያልነበራቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስም 48 በመቶ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የቫይረሱ ስርጭት እንደየክፍለ ከተሞቹ የሚለያይ ቢሆንም ቀደም ሲል የተጠቀሰው ታሪክ ከሌላቸው ታማሚዎች ውስጥ 45ቱ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ቫይረሱ ከሰው ወደሰው እየተዛመተ የሚገኝበትን ፍጥነት ለማሳየትም በልደታ ክፍለ ከተማ በአንድ ሰው አማካይነት 32 ሰዎች መያዛቸውን አንስተዋል ዶክተር ኤባ፡፡

በሌላ በኩል በፖሊስ ጣቢያ በህግ ታራሚዎችና ጉዳያቸውን በሚያስፈፅሙ ሰዎች መካከል በተፈጠረ ንኪኪ በአንድ የቫይረሱ ታማሚ ምክንያት ሌሎች 66 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮኃንስ ጫላ እንደተናገሩት፥ የሃገሪቱም ሆነ የአፍሪካ ትልቁ የመገበያያ ስፍራ የሆነው መርካቶ ገበያን በያዘው አዲስ ክፍለ ከተማም ቁጥሮች በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።

በመሆኑም ከፍተኛ ጥግግትና ጥንቃቄ አልባ እንቅስቃሴን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ ሁለተኛው የቤት ለቤት ልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያመላከቱት ሃላፊው፥ በልየታ ስራ ወቅትም ተመሳሳይ የጉዞም ሆነ የንክኪ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች መገኘታቸውን በማንሳት አሳሳቢነቱን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

በመግለጫው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በተለይ በመዲናዋ ስጋትነቱ እየጨመረ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን እስካሁን በ7 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተከሰተውን ይሄው የቫይረስ የስርጭት አድማሱን በክልሎች በተለይም ከአጎራባች ሃገራት ወደ ሃገር በሚገቡ ታማሚዎች አማካይነት ይበልጥ እንዳይስፋፋ የክትትል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑም ተነስቷል፡፡

በቀጣይ ቀናትም የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚያከብሩት የኢድ-አልፈጥር በአል ስለሚመጣ በግብይትና በበአሉ አከባበር ወቅት ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዳይለየው መልዕክት ተላልፏል፡፡

በሶዶ ለማ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.