Fana: At a Speed of Life!

የልማት ድርጅቶች የገበያ ፍላጎትን መፍጠር የሚችል አሠራር መከተል እንዳለባቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የልማት ድርጅቶች የገበያ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ የገበያ ፍላጎትን መፍጠር የሚችል አሠራር መከተል እንዳለባቸው የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን አስገነዘቡ።

የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2016 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ጌቴ፣ የልማት ድርጅቶች የሥራ ኀላፊዎች እና የቦርድ አባላት ተገኝተዋል።

የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አበባው ጌቴ በመድረኩ ላይ፤ ድርጅቶች ኅልውናቸውን ከማስቀጠል ጀምሮ ለተቋቋሙለት ራዕይ ስኬት የሚያስፈልጓቸውን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው የልማት ድርጅቶች የገበያ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ የገበያ ፍላጎትን መፍጠር የሚችል አሠራር እንዲከተሉ አስገንዝበው፤ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

ድርጅቶቹ በቴክኖሎጂ ሽግግርና አሠራር ተሞክሮ መቀመሪያ ሆነው እንዲገኙም ሊሠራ ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከመደበኛ የልማት ስራዎች ባለፈ በተቆርቋሪነትና ውጤታማነት እንዲገነቡ፤ ሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካም የልህቀት ማዕከል እስከመሆን የዘለቀ ራዕይ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ 13 የልማት ድርጅቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.