Fana: At a Speed of Life!

ገፅታውን በመቀየር ሴት መስሎ በመቅረብ ከአንዲት ግለሰብ ላይ 103 ሺህ ብር አታሎ የወሰደው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ገፅታውን በመቀየር ሴት መስሎ በመቅረብ ከአንዲት ግለሰብ ላይ 103 ሺህ ብር አታሎ የወሰደው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

ቺና በሚል ስም በሴት ፆታ የሚጠራው ግለሰብ በሜካፕ እና በሌሎች ነገሮች ራሱን የሴት ገፅታ አላብሶ ሲንቀሳቀስ እንደነበርና ኳታር እና እንግሊዝ ሃገር እንደኖረ አረብኛ እና እንግሊዘኛም አቀላጥፎ እንደሚናገር የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያመለክታል ፡፡

የግል ተበዳይ የሆነችው እየሩሳሌም ሰሎሞን በጓደኛዋ አማካይነት ቺናን እንደተዋወቀችው እና ወደ ውጪ ሀገር ወስዶ ስራ እንደሚያስቀጥራት የነገራት መሆኑን በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የራስ ደስታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ታምሩ መሮ ገልፀዋል።

እስከዚያው በጋራ ሱፐር ማርኬት ከፍተው እየሰሩ እንዲቆዩ ጠይቋት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ቅርርብም ቺና ከአከራዩ ጋር እንዳልተስማማ እና ሌላ ማረፊያ ቤት እንደሚፈልግ ሲያማክራት እየሩሳሌምም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ዘበኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ዩፍቲኒ ፔንሲዮን ይዛው መጥታ እዚያ እንዲያርፍ ማድረጓን መርማሪው አስረድተዋል ፡፡

በጋራ ሱፐር ማርኬት ለመክፈት የተነሳውን ሃሳብ በተመለከተም ቺና እየሩሳሌምን ብር እንድታመጣ ሲጠይቃት ከተለያዩ ሰዎች በብድር ያገኘችውን 103 ሺህ ብር ትሰጠዋለች፡፡
እሱም የቀረውን እኔ እጨምርበታለሁ ብሎ ይቀበላታል፡፡

ከዚያ በኋላ ሰልኩን ዘግቶ ከፔንሲዮኑን ለቆ የወጣው ግለሰቡ ግለሰቧ ጥቆማ በመስጠቷ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፓሊስ ገልጿል።

የሴት ገፅታ ተላብሶ የተያዘው ቺና በፖሊስ በተደረገው ማጣራት ወንድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.