Fana: At a Speed of Life!

በቅርቡ የተከበሩ በዓላትን እንዲሁም ብሄራዊ ሁነቶችን ተገን በማድረግ ጸረ ሰላም ሀይሎች ለመፈፀም ያሴሩትን የሽብር ዕቅድ ማክሸፍ መቻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በቅርቡ የተከበሩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት እንዲሁም ብሄራዊ ሁነቶችን ተገን በማድረግ ጸረ ሰላም ሀይሎች ለመፈፀም ያሴሩትን የሽብር ዕቅድ ማክሸፍ መቻሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በ2016 ዓ.ም በተከታታይ የተከበሩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት እንዲሁም ብሄራዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ክፍሎች የምስጋናና ዕውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃግብሩ የተገኙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት÷ የአዲስ ዓመት መባትን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአደባባይ በተለያዩ አካባቢዎች የታደሙባቸው ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት እንዲሁም ብሄራዊ ሁነቶች ተስተናግደዋል።

እነዚህን ሁነቶች ለማደናቀፍ ፀረ-ሰላም ቡድኖች የተቀናጀ ርብርብ አድርገዋል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ስልጠና ከተጠናቀቀ በየደረጃው ያለ ኃላፊ ሀገር ማጽናት የሚያስችለውን አቅም ያጎለብታል በሚል ስሌት ስልጠናውን ፀረ-ሰላም ቡድኖች ለማደናቀፍ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ የተደገፈ ከፍተኛ ርብርብ አድርገው እንደነበር አመልክተዋል።

ይሁንና የእነዚህን ቡድኖች ሴራ ለማክሸፍም የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት አመራሮችና አባላት ከመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ጋር በየጊዜው የሚመጡ መረጃዎችን በማቀናጀት እና በመተንተን መረጃዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራ ማከናወናቸውን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

በዚህም የጠላት ዕቅድ እንዲከሽፍና ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና የተለያዩ ሁነቶች በሰላም እንዲከበሩ ተደርጓል ብለዋል።

በአማራ ክልል በፋኖ ስም የሚነግደውን ዘራፊና ጽንፈኛ ቡድን እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ደግሞ የሸኔ ሽብር ቡድን በተደጋጋሚ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት እንዲሁም ብሄራዊ ሁነቶችን ለመበጥበጥና ሁከት ለመፍጠር ጥረቶች ቢያደርጉም እንዳልተሳካለቸው የገለፁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ክፍሎች አመራሮችና አባላት ላደረጉት ያልተቋረጠ ድጋፍና ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ዘራፊና ጽንፈኛ ኃይል በቅድሚያ ክልሉን ከዛም የፌዴራል ስርዓቱን ለማፍረስ ያቀደና ያለመ ኃይል መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን፤ ለዚህም ሰነድ አዘጋጅቶ እና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ስልት ነድፎ ከተሞችን የመቆጣጠርና ሰላም የማደፍረስ እልፍ ሲልም የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የተንቀሳቀሰ ቡድን መሆኑን አመልክተዋል።

ሆኖም ግን ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በተሰሩ ስራዎች በአጠረ ጊዜ በክልሉ የነበረው የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ መሻሻል እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

የጥፋት ኃይሉ በክልሉ ውስን ቀበሌዎችና ወረዳዎች ላይ እየተሹለከለከ ወደተራ የሽፍትነትና የደፈጣ ጥቃጦች የመሰንዘር ተራ ውንብድና ውስጥ የገባ መሆኑን ጠቅሰው ለክልሉ አንጻራዊ ሰላም ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፌደራልና የክልሉ መንግስት ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሌት ተቀን ለሰራችሁ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ምስጋና ይገባችዋል ብለዋል።

በአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅና የጸጥታ ችግር ሲገጥም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሽብርተኛው የሸኔ ቡድን በንፁሃን ላይ ግፍ ለመፈፀም ቢሞክርም በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፌደራልና የክልሉ መንግስት ፀጥታ አካላት የማያዳግም እርምጃ እንደተወሰደበት አቶ ተመሰገን ጥሩነህ ገልፀዋል።

ይህም ውጤት የተገኘው የደኅንነት እና የጸጥታ ተቋማት በጋራ ተናበው መስራት በመቻላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ እንዳመለከተው÷ ህዝቡ የራሱንና የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ረገድ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሁሉም ፀጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም እያሳየ ያለውን ድጋፍ እንደተለመደው አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.