Fana: At a Speed of Life!

ጆ ባይደን የእስራዔል-ሃማስ ጦርነት “ጋብ” እንዲል ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የእስራዔል-ሃማስ ጦርነት “ጋብ” እንዲል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባይደን የተኩስ አቁም ጥሪያቸውን ለሁለቱ ወገኖች ያስተላለፉት በሚኔሶታ ተገኝተው 200 ለሚጠጉ ደጋፊዎቻቸው የገጠር ልማት ላይ የቅስቀሳ ንግግር እያሰሙ ባለበት ወቅት ባጋጠማቸው ያልታሰበ ተቃውሞ መሆኑን ዴይሊ ኒውስ አስነብቧል፡፡

በመድረኩ በእስራዔል እና ሃማስ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከመርገብ ይልቅ እየተካረረ እና የበርካቶችን ንጹሐን ሕይወት እየቀጠፈ መምጣቱ ያሳሰባት አንዲት ሴት “አሁኑኑ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ያስተላልፉ” ስትል ንግግራቸውን አቋርጣቸዋለች፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደንም “ጦርነቱ ጋብ ማለት ያለበት ይመሥለኛል ፤ ጋብ ማለት አለበት ስል እስረኞችን ለማስወጣት ማለቴ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ኋላ ላይ ባይደን “እስረኞች” ሲሉ የገለጹት በሃማስ የታገቱትን ሰዎች ለማለት መሆኑን ኋይት ሐውስ ግልፅ አድርጎታል፡፡

ባይደን ከሴትዮዋ ጋር ተጨማሪ ጊዜ መውሰዳቸውንና በጉዳዩ ላይ ከእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ቤታንያሁ ፣ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ እና ከሃማስ ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች መምከራቸውን እንዳስረዷትም ተጠቁሟል፡፡

ባይደን ዝም ብለው እንዳልተቀመጡ፣ይልቁንም ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባ ፣ በጦርነቱ ችግር ውስጥ ያሉ ንጹሐን በግብፅ በኩል ነጻ የመውጫ ቀጣና እንዲያገኙ እንዲሁም በፍልሥጤሙ ተቃዋሚ ቡድን የታገቱ ሁለት አሜሪካውያን እንዲለቀቁ ሲሰሩ መቆየታቸውንና ከሞላ ጎደል ውጤት ማምጣቱን ገልጸውላታል ነው የተባለው፡፡

ነጩ ቤተ-መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ እንዲገባ ፣ ንጹሐን ነጻ የመውጫ በር እንዲያገኙ እንዲሁም ታጋቾች እንዲለቀቁ ጥረት መደረጉን አስረድቷል፡፡

ነገር ግን ጦርነት በማቆም ጉዳይ ላይ ፈቃዱ ያለው በሃማስ እጅ ነው በሚል ሰበብ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመሥጠት ተቆጥቧል ነው የተባለው፡፡

የእስራዔል እና ሃማስ ጦርነት ዛሬ 27ኛ ቀኑን ይዟል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.