Fana: At a Speed of Life!

ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ከ 1 ሺህ በላይ ሰዎች በተሃድሶ ስልጠና ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ጋር በተያይዘ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ 1 ሺህ 52 ሰዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ዋና የችግሩ ተዋናዮችን ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 3 ሺህ 200 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያው 1 ሺህ 52 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በመረጃ እጦት፣ በተዛባ መረጃ፣ በመደናገር፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወደዚህ ተግባር የገቡ እና የተፀፀቱ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ተጠርጣሪዎች በሁለተኛ ዙር 931 ሰዎች የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንደየ ሁኔታው እነዚህም ወደ ቤተሰባቸው ይቀላቀላሉ ብለዋል፡፡

317 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

304 ደግሞ በደረቅ ወንጀል የሚጠየቁ መሆናቸውን ገልፀው እስካሁን ማረሚያ ቤት የገቡት 11ተጠርጣሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ እንደገመገመውም ሊፈርስ ተቃርቦ የነበረው ክልል ከመፍረስ መታደግ መቻሉን፣ አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሰዋል፤ የህዝቡ የሰላም ፍላጎትና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ያለው የሰላም ቁርኝት በእጅጉ ጨምሯል፤ ህዝቡ ለፀጥታ ሃይሉ የሚያደርገው ድጋፍ በሚያኮራ መንገድ ጨምሯል፤ ክልሉ በአዲስ ብቁ አመራሮች ተተክቷል ብለዋል፡፡

እዙ በዚህም ክልሉን ከመፍረስ ለታደጉ ከእዚህም በላይ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ እና ሰላም እንዲረጋገጥ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና ማቅረቡንም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግስት በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች እና በዝናብ ማጠር ምክንያት የተፈጠሩ የምግብ እጥረቶችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.