Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በይፋ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በይፋ ስራ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መርጋ ዋቅወያ እና የፈንዱ የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ሰለሞን ደስታ የመድን ፈንዱ ስራ መጀመርን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ሰለሞን ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የፈንዱ ስራ ከለውጡ በኋላ በፋይናንስ ዘርፉ ሪፎርም ከተገኙ ስኬቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2013 ዓ.ም ፀድቆ ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ደንብ ፈንዱን ማቋቋም ያስፈለገው በኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት የሀገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ በማድረግና ለማጠናከር እንዲቻል መሆኑን ያመላክታል።

በደንቡ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፈንዱን በበላይነት የሚመሩ አምስት የቦርድ አባላትን መሾማቸው ይታወቃል።

ፈንዱ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማኅብረሰብ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ አደጋ ቢያጋጥም አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ስርዓት እንደሆነም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፈንዱ ገንዘብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ሂሳብ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን÷ ሁሉም አባል የፋይናንስ ተቋማት በፈንዱ የሚወሰነውን መነሻ የዓረቦን ክፍያ ወደ ፈንዱ ሂሳብ ገቢ ያደርጋሉ።

መንግሥትም መነሻ ካፒታል እንዲሆን ለፈንዱ 200 ሚሊየን ብር እንደሚመድብ ደንቡ ደንግጓል።

ፈንዱ የዓረቦን ክፍያዎችን ከአባል የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ መዋጮዎችን እንደ መንግስትና የልማት አጋሮች ካሉ ሌሎች ምንጮች መሰብሰብና ወደ ራሱ ገቢ ማድረግ እንደሚችል ስልጣን ተሰጥቶታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.