Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ኩባ ላይ የጣለችውን የንግድ ማዕቀብ እንድታነሳ ተመድ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ኩባ ላይ የጣለችውን ለአሥርት ዓመታት ያኅል የዘለቀ የንግድ ማዕቀብ እንድታነሳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለ31ኛ ጊዜ ጠየቀ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔውን በትናንትናው ዕለት አካሂዷል፡፡

ጉባዔው ኩባ አሁን ላይ ካለፉት አሥርት ዓመታት ይልቅ እጅግ አስከፊ ለሆነ የምጣኔ ሐብት ቀውስ እንደተዳረገች አንስቶ መፍትሄ እንዲሰጥበት ጠይቋል፡፡

ሀገሪቷ በምግብ ፣ ነዳጅ እና መድሐኒት አቅርቦቶች እጥረት እየተቀጣች እንደምትገኝም ነው ያስገነዘበው፡፡

ኩባ ላይ የተጣለውን የንግድ ማዕቀብ አሜሪካ እንድታነሳ 187 የተመድ አባል ሀገራት ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን እስራዔል እና አሜሪካ ግን ተቃውመዋል።

በጉባዔው ዩክሬን ድምፀ ተዓቅቦ ማድረጓን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ በጉባዔው ባደረጉት ንግግር ÷ ” ኩባ ላይ የተጣለው የንግድ ማዕቀብ ÷ የምግብ፣ የመድሐኒት ፣ የቴክኖሎጂ እና ሕክምና ቁሶች ወደ ሀገሪቷ እንዳይገቡ መሰናክል ሆኗል ” ብለዋል።

የወጭ ንግዷንም ወደ ጎረቤት አሜሪካ እንዳትልክ ማዕቀቡ እንቅፋት መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ኩባ በፈረንጆቹ 2022 ብቻ ከወጭ ንግድ ማግኘት የሚገባትን 5 ቢሊየን ዶላር እንዳጣችም አስረድተዋል።

ሮድሪጌዝ አክለውም በጉዳዩ ላይ አሜሪካ እያራመደች ያለው ፖሊሲ ሆነ ብላ በኩባ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደርና በግዳጅ ከሥልጣን ለማስወገድ ነው ብለዋል፡፡

የጋቦን እና የፔሩ ተወካዮች ከኩባ ጎን የቆሙ ሲሆን በንግግራቸው አሜሪካ እየተከተለች ያለው ፖሊሲ ከተመድ ሰብዓዊ መርኆዎች ውጪ ነው ብለዋል ፤ ማዕቀቡ እንዲነሳም ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.