Fana: At a Speed of Life!

“ሠራዊቱ በወገኖቹ የተካደበትን ቀን ሁሌም እንዳይደገም እንዘክረዋለን” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “እንዳይደገም ሁሌም እንዘክረዋለን” በሚል መሪ ሐሳብ ሰሜን ዕዝ የተጠቃበት ሦስተኛ ዓመት የመታሰቢያ መርሐ -ግብር ተካሂዷል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “ቀኑ ድንበር እየጠበቀ፣ ሠብል እየሰበሰበ፣ የአንበጣ መንጋ፣ እያባረረ እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ በመከላከሉ መርሐ-ግብር ተሳትፎ የበኩሉን ያበረከተ ሠራዊት በወገኖቹ ተክዶ ጥቃት የተፈፀመበትን እና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡

ቀኑ ለግል ሥልጣንና ጥቅም ሲሉ ዘርና ወገን ለይተው ራሳቸው ባደራጁት ኃይል የራስን ጠባቂ እና ጋሻ የሆነ ሠራዊት በጭካኔ በመጨፍጨፍ ሀገርን ያለጠባቂ ለማስቀረትና መንግሥትን ለመጣል ሙከራ የተደረገበትመሆኑንም አንስተዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል ትምሕርት ቤቶችን፣ የጤና ኬላዎችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እየሠራ እና እያስፋፋ ዐቅም የሌላቸውን ተማሪዎች አስተምሮ ለቁም ነገር ሲያበቃ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጋር ተዛምዶ፣ ተዋልዶና ቤተሰብ ሆኖ በኖረበት ክልል በፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ምክንያት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በሠራዊቱ ላይ መፈፀሙን ነው የጠቀሱት፡፡

ከዚህ ታሪክ መላው ኢትዮጵያዊ ተምሮ እንዳይደገም ዛሬም ነገም ሁሌም ይዘከራል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገፅ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ጦርነቱ በሁሉም ወገኖች ላይ ያደረሰው ጉዳት የኢትዮጵያ ጉዳትና መከራ በመሆኑ ሁሌም እንደሚዘከር በአጽንኦት ገልጸው÷ ሁሉም ሕዝብ ለሠላም እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው÷ “ጥቅምት 24 ቀንን መዘከር ትልቅ ትርጉም አለው፤ በተፈጠረው ነገር ከልባችን ተፀፅተን ለሠላም በኅብረት ልንተጋገዝ ይገባል” ብለዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.