Fana: At a Speed of Life!

‘ከዕዳ ወደ ምንዳ’ በሚል ለምክር ቤት አባላት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)’ከዕዳ ወደ ምንዳ’ በሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ10 ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ምክትል አፈ ጉባኤዋ ሎሚ በዶ÷ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ባለመረዳትና ባለማወቅ በዕዳ ስትፈትን መቆየቷን አንስተው የሀገርን ሀብት በማወቅ ወደ ምንዳ መቀየር የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ለውጥን ለማሳካት፣ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግና የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በእውቀትና በጥበብ መትጋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተለይም የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚው አካል ፖሊሲና የስትራቴጂ በሚያወጣበትና በሚተገብርበት ወቅት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየት እንዲሁም ለውጥን በማረጋገጥ ሂደት የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አክለውም የተቋማትን ሃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር ያስተሳሰረ የግምገማ ስርዓት በመከተል ችግሮች ወደ እድል እንዲቀየሩ ከተለመደው አሰራር ውጪ መትጋትም ከምክር ቤት አባላት ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለዚህም ሀገርን የማያሻግሩ ኋላ ቀር አሰራሮችና የሀሰት ሪፖርቶች ላይ ጠንካራ የክትትል ዘዴን መተግበርና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ እርምጃ መውሰድ ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው ብለዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው÷ ከተሰጣቸው ስልጣንና ሃላፊነት ባለፈ እንደ አንድ ዜጋ ስራዎችን በተለየ ፍጥነትና ጥራት ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ስልጠናው የምክር ቤቱ አባላት ሀገራዊ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው የህዝብ ውክልና ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አጋዥ መሆኑም ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.