Fana: At a Speed of Life!

ሊቢያ 600 ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ግብፃውያን ወደሀገራቸው ልትመልስ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሊቢያ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ 600 ሰነድ አልባ የግብፅ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ልትመልስ መሆኗ ተገልጿል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሊቢያ የሚገኙ ፍልሰተኞችን ወደ አሀራቸው የመመለስ ሃላፊነት የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንደነበር ነው የተገለጸው።

በቅርቡ ሊቢያን በሚያስተዳድሯት ሁለቱ አስተዳደሮች መካከል ከተደረሰው ስምምነት በኋላ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ጋር ግንኙነት ያለው ህገ ወጥ ስደት መከላከያ ዳይሬክቶሬት ፍልሰተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ኃላፊነትን መውሰዱ ተጠቁሟል።

ህገወጥ የግብፅ ፍልሰተኞች ቡድን ወደ ሊቢያ ግዛት በህገ ወጥ መንገድ በመግባታቸው አሁን ካሉበት ከህገወጥ ስደት መከላከያ ዳይሬክቶሬት ቅጥር ግቢ ወደ መጡበት እንዲመለሱ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው።

ፍልሰተኞቹ በአብዛኛው ወንዶች እንደሆኑና 1 ሺህ 375 ኪሎ ሜትር ርቀት በአውቶቡሶችተጉዘው ወደ ግብፅ እስማድ ማቋረጫ እንደሚደርሱ ተነግሯል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ግብፃውያን በሊቢያ ለዓመታት የኖሩ ሲሆን አንዳንዶቹ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር አስበው እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡

በርካቶችም እዛው ሊቢያ ውስጥ በግብርና፣ በግንባታ እና በሌሎች ዘርፎች በመስራት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ተጠቁሟል።

የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በየአመቱ በባህር ወደ አውሮፓ ለመግባት ለሚፈልጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ማዕከል መሆኗ ይነገራል።

የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት በዚህ ዓመት ከግንቦት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ከ700 ሺህ በላይ ፍልሰተኞች በሊቢያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ መግለፁን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.