Fana: At a Speed of Life!

የአርቲስት አሊ ቢራ ህይወት ያለፈበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ-ስርዓት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርቲስት አሊ ቢራ ህይወት ያለፈበት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ-ስርዓት በተለያዩ ዝግጅቶች በድሬዳዋ ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ አካባቢ በተዘጋጀ የአርቲስቱ የቢልቦርድ ምርቃት የጀመረው የመታሰቢያ ዝግጅት ትናንት ምሽት በጧፍ ማብራት ሥነ-ስርዓት ቀጥሏል።

በመታሰቢያ ስነ -ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፥ አርቲስት አሊ መሐመድ ሙሣ (አሊ ቢራ) ዕድሜውን በሙሉ ለሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት ሲታገል እንደነበር ገልጸዋል ።

ድሬዳዋ ካፈራቻቸው ድንቅና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ከሰሩ አርቲስቶች መካከል አርቲስት አሊ ቢራ ቀዳሚው እንደነበርም ተናግረዋል።

አሊ ቢራ ጭቆናንና ኢ -ሰብአዊ ድርጊትን በአፅንኦት የሚጠየፍና ሰው በእኩልነት እንዲኖር የተጋ ድንቅ አርቲስት እንደነበር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አርቲስት አሊ ቢራ በሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቋንቋዎች ባቀነቀናቸው 300 የሚጠጉ ድንቅ ዘፈኖቹ አዲሱ ትውልድ ለቆመለት አንድ ዓላማና ግብ ሳይታክት መታገል እንዳለበት ማስታማሩን አውስተዋል።

አርቲስቱ በጥበብ ሥራዎቹ ያበረከታቸውን የጥበብ ውጤቶች ለማስታዎስ የሚያግዙ ቋሚ መታሰቢያ ተቋማት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መቋቋማቸውን አድንቀው፣ አስተዳደሩም ተመሳሳይ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው÷ አርቲስት አሊ ቢራ መስዋዕትነት በመክፈል ባቀጣጠለው የነፃነትና የእኩልነት ችቦ የአሁኑን ትውልድ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል” ብለዋል።

በመታሰቢያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአርቲስቱን ባለቤት ሊሊ ማርቆስን ጨምሮ ከሀገርና ከውጭ ሀገራት የመጡ የአርቲስቱ ወዳጆችና ጓደኞች፣ አርቲስቶች እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የአርቲስት አሊ ቢራ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀጥል ታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.