Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና ግብዓት ምርት ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የተመራ ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች እና የባለሙያዎች ቡድን በሁለተኛው ዓለም አቀፍ የሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና ግብዓት ምርት ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

“የአፍሪካ የሀገር ውስጥ የምርት ፍላጎትና የተቀመጡ ስትራቴጂክ ግቦች እንዲሳኩ መደገፍ” በሚል ርዕስ የተካሄደን የፓናል ውይይት የመሩት ዶ/ር ሊያ፤ በኢትዮጵያ የህክምና ግብዓትና መሣሪያዎች ምርትን ለማስፋፋትና ለማበረታታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በአፍሪካም የሀገር ውስጥ ምርትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ሰፊ ውይይት መደረጉንም ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም ከዓለም የጤና ደርጅት ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድሃኒት ባለስልጣን ማቹሪቲ ደረጃ 3 ለመድረስ እያደረገ ያለውን ጥረት፣ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች ምርታቸውን በአለም ጤና ድርጅት ፕሪኳሊፋይ ለማስደረግ የሚሰራውን ስራ እንዲሁም የሀገሪቱ የ10 አመት ብሄራዊ የመድሃኒት ምርት ልማት ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የክትባት ማምረቻ ፕሮጀክት የደረሰበትን ደረጃ እና ስለ ሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅም ግንባታ ከተለያዩ የልማት አጋሮች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተወያይተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.