Fana: At a Speed of Life!

‘ሂዩማን ዌል ፋርማሲቲካል’ የተባለ የቻይና ኩባንያ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ‘ሂዩማን ዌል ፋርማሲቲካል’ የተባለ በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት የተሰማራ የቻይና ኩባንያ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

ኩባንያው ድጋፉን ያደረገው ከንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከምግብ፣ መጠጥና መድሃኒት ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት መሆኑ ተገልጿል።

በድጋፉ ሙቀት መለኪያን ጨምሮ ሌሎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን  የተካተቱበት መሆኑ ተነግሯል።

የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ታንግ ዩዦንግ ድጋፉን ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ማስረከባቸው ተገልጿል።

ሚኒስትሯ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ የስራ ላይ መከላከያ ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ መሆኑን  ተናግረዋል።

የተደረገው ድጋፍ በዋናነት ወረርሽኙን ለመዋጋት ከፊት ለፊት የተሰለፉ የጤና ባለሙያዎችን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ጠቀሜታው ድርብ እንደሆነም ነው ያብራሩት።

በቀጣይም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የስራ ላይ ደህንነት መከላከያ ቁሳቁሶቹ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እንደሚሰራ ዶክተር ሊያ አንስተዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየስ ÷ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየተፋለሙ ያሉትን የህክምና ባለሙያዎችን መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ኩባንያው ያደረገው ድጋፍ ጉልህ ሚና እንዳለውም ማንሳታቸውን ነው የተነገረው።

የቫይረሱ ስርጭት በዋነት የማኑፋክቸሪንግ ክፍለ ኢኮኖሚን እንደሚያዳክመው ገልጸው÷ መንግስት ጉዳቱን ለመቀነስ የተለያዩ አማራጮችን እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም በዘርፉ የተሰማሩ ሰራተኞችን ደህንነት በመጠበቅ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማድረግ በትኩረት ከሚሰሩ ጉዳዮች አንዱ   መሆኑን ገልጸዋል።

የኩባንያው ስራ አስኪያጅ  ታንግ ዩዦንግ  በበኩላቸው÷ ኩባንያው 20 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ በኢትዮጵያ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን እያመረተ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም የኢንቨስትመንት ካፒታሉን ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ውጥን መያዙን አስረድተዋል።

”ኩባንያው የህክምና ቁሳቁሶች አምራች እንደ መሆኑ መጠን ማህበራዊ ሃላፊነት እንዳለበት እንረዳለን” ያሉት ታንግ ዩዦንግ÷ የኩባንያው ድጋፍ ይህንን ማህበራዊ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ ያስገባ  ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.