Fana: At a Speed of Life!

የ5 ሺህ ቤቶች ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል-ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተማ አስተደዳሩ በጀት ግንባታቸው የተጀመሩ የ5 ሺህ ቤቶች ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ÷ ዛሬ በሁለተኛ ቀን የፕሮጀክቶች ጉብኝት የሁለት ሪፈራል ሆስፒታሎች፣ የቤቶችንና የላፍቶ የገበያ ማዕከል ግንባታ ያለበትን ደረጃ ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት ሆስፒታሎች የላቁ እንደሆኑ የገለጿቸው፤ የቤተል-መንዲዳ ሪፈራል ሆስፒታል እና የላፍቶ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታቸው በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል።

የሆስፒታሎቹ ግንባታ ሲጠናቀቅም ከሚሰጡት ማህበራዊ ፋይዳ በተጨማሪ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጉ ይሆናል ሲሉም አክለዋል።

በከተማዋ ያለውን የቤት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ በከተማ አስተደዳሩ በጀት ግንባታቸው የተጀመሩ የ5 ሺህ ቤቶች ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አንስተዋል፡፡

የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች ውስጥ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ 400 ቤቶችን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

ለከተማዋ 4ኛው የገበያ ማዕከል የሆነውና 144 ሱቆች እና 14 መጋዘኖች የተካተቱበት የላፍቶ ምዕራፍ 2 የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከልም በቀጣይ 90 ቀናት ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅም ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ የገበያ ሰንሰለቱን በማስተካከል አምራችን በቀጥታ ከሸማች ጋር በማገናኘት የአዲስ አበባን ህዝብ የኑሮ ጫና የማቃለል ስራን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.