Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ያካሂዳል

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በነገው ዕለት ያካሂዳል።

ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን እንዳለው በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 17 ተደንግጓል፡፡

በዚህ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በነገው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በመገኘት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያቀረቡትን የፌደራል መንግስቱን ዓመታዊ ዕቅድ የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሚሰጡ ይሆናል።

ምክር ቤቱ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በነገው ዕለት በሚካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የሐይማኖት አባቶች ተወካዮች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪዎች፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.