Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያንን በጋራ የሚያስተሳስር ዐቢይ ትርክት ለመገንባት ብልፅግና ፓርቲ በአርዓያነት ይሰራል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያንን በጋራ የሚያስተሳስር ዐቢይ ትርክት ለመገንባት ብልፅግና ፓርቲ በአርዓያነት እንደሚሰራ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አደም ፋራህ÷ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ለዘመናት የሀገራቸውን ክብርና ሉዓላዊነት አስከብረው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የሀገርና የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም የሰለጠነ ፖለቲካ ስርዓት አለመገንባቱን ነው የገለጹት።

በመሆኑም በሀገርና ሕዝብ ጉዳይ በጋራ የመስራት ባህልን ለማዳበር እና በሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ ጤናማ የሀሳብ ፉክክር ለማድረግ የፖለቲካ ድባቡን ማሻሻል ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ እንደ ዕዳ ከሚቆጠሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል ፍጹማዊ አንድነትና ፍጹማዊ ልዩነት ላይ ያተኮሩ ነጠላ ትርክቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ለሁሉም የምትመች የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና የህዝብን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር የጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንባት ተገቢ በመሆኑ ወደ ስራ መገባቱን በመጥቀስ።

ብልፅግና ፓርቲ ትናንትን በአግባቡ በመገምገም ለመጻኢ ጊዜ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የህዝብን እህትማማችነትና ወንድማማችነት በማጠናከር የሀገር ግንባታን ማፋጠን እንደሚገባ የሚያምንና ለስኬቱም የሚተጋ ፓርቲ መሆኑንም አብራርተዋል።

ለሀገር ይጠቅማሉ ብሎ ያዘጋጃቸው እሳቤዎች፣ እቅዶች፣ እሴቶችና መርሆዎች ትግበራ ከፓርቲው አመራርና አባል ሊጀመር ይገባል ብሎ እንደሚያምንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበሩ፣ የፍጹማዊ አንድነትና ልዩነት ትርክት መንሰራፋቱና ኋላቀር የፖለቲካ አካሄድ መኖሩ የጋራ ትርክትን የመገንባት ሂደትን እንደሚፈትነው ተናግረዋል።

የፓርቲው አመራርና አባላትም ለፈተናዎች ሳይበገሩ የሚፈለገውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ጠንካራ ትግል መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የብልፅግና አመራርና አባላት ለጋራ ብሔራዊ ትርክትና ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥ በአርዓያነት ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ አፈጻጸሙ በየጊዜው እየተገመገመ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ የሚያደርግ አቅም ግንባታ ስራ እንደሚከናወንም ነው ያነሱት።

ፓርቲው ላስቀመጣቸው ግቦችና ለሀገር ርዕይ መሳካት ሁሉም የዓላማ ፅናት፣ የተግባርና የአመለካከት አንድነት በመያዝ መስራት እንደሚገባውም ገልጸዋል።

ሆኖም በዚህ ሂደት ከስህተቱ የማይማር፣ የጋራ እሴቶችንና የፓርቲውን መርሆ የማያከብር አመራርም ሆነ አባል ካለ ተገቢውን ማጥራት በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.