Fana: At a Speed of Life!

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ መሰብሰብ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪዎቹ 10 ቀናት በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ መሰብሰብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስተናግዱም ነው የትንበያ መረጃዎች ያሳዩት፡፡

በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ በሚገኙ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ተመላከቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኦሮሚያ ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ አርሲ ሁሉም የባሌና ጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ፣ የቦረና ዞን፣ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ ጎንደር፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማም መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ተጠቁሟል።

ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚያገኙ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ኢንስቲትዩቱ ያሳሰበው፡፡

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል፣ መካከለኛው ኢትዮጵያ፣ የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ምስራቅ ጎጃም፣ የማዕከላዊና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብና የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 3፣ ዞን 5፣ ዞን 4 እና ዞን 1 ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖራቸው በትንበያው ተገልጿል።

በበጋ ሁለተኛው የዝናብ ወቅትን የሚያስተናግዱ በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው እርጥበታማ የአየር ጸባይ ሁኔታ በደጋ አካባቢ ለተዘሩ ሰብሎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተጠቅሷል፡፡

በአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የእጽዋት ልምላሜን ለማሻሻል፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የውሀ ምንጮችን ለማጎልበት እና ለእንስሳት የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሀ አቅርቦትን ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተመልክቷል፡፡

በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለጓሮ አትክልቶች፣ አርሶ አደሩ ለሚዘራቸው የጥራጥሬ ሰብሎች እና ወቅቱን ጠብቀው ላልተዘሩና እድገታቸው ገና ለሆኑ ሰብሎች በበቂ ሁኔታ ውሀ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚኖረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በአፋጣኝ መሰብሰብ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አስጠንቅቋል።

በገናሌ ዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ መካከለኛውና ታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛውና መካከለኛው ዓባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ በታችኛው ተከዜ ተፋሰሶች የሚኖረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ የውሃ ሀብትን ለማሻሻል አወንታዊ ሚና ቢኖረውም÷ የጎርፍ ተጋላጭነትን ሊያስከትል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.