Fana: At a Speed of Life!

በከተማ ደረጃ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ እና የህብረተሰብ ተሳትፎ ንቅናቄ ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተማ አቀፍ ደረጃ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የገቢ እና የህብረተሰብ ተሳትፎ ንቅናቄ ስራ ተጀመረ።

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ እና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ትግል እውን ማድረጊያ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ግድቡ የመተባበር ተምሳሌት ጭምር በመሆኑ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ከዚህ ቀደም ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዘመን ጆነዲ በበኩላቸው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአስሩም ክፍለ ከተሞች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የህብረተሰቡን ድጋፍ እና ተሳትፎ ለማጠናከር የገቢ ማሰባሰብ እና ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በዚህም ከ500 ሺህ በላይ የከተማዋን ነዋሪ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በማሳተፍ እስከ 100 ሚሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ እና የህዝብ ተሳትፎ መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አበበች ነጋሽን ጨምሮ የካቢኔ አባላት የተገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር እና አባላት የ200 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ በመፈጸም ድጋፍ ማድረጋቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.