Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ማንንም ለመጉዳት አይደለም – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው የዲፕሎማሲ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሰጡት ማብራሪያም ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏን አስመልክቶ ባደረጉት ገለጻ፥ የዲፕሎማሲ ዋና መስፈሪያ ሚዛኑ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከሌሎች ጋር በሚኖር ትብብር እና ስምምነት የሚፈጸም መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

የፖሊሲያችን መነሻዎችም ብሄራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት፣ (መልክዓምድራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚካዊ) ትሩፋቶችን እንከተላለን፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ማንንም ደግፋ እና ተቃውማ አልያም ማንንም ለመጉዳት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብሪክስ የደቡብ ደቡብ ኮርፖሬሽን ተቋም መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሌሎች ሀገራት ባቀረቡት ጥያቄ እንዲሁም ኢትዮጵያ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ቡድኑን መቀላቀሏን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ለእኛም ለብሪክስም ጠቃሚ ነው በሚል የተደረገ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርቡም ከሩቁም ተስማምታና ተባብራ ማደግን የምታስቀድም ሀገር ስለሆነች ፖሊሲያችን ባስቀመጠው መሰረት መታየት ያለበት በዚያው አግባብ ነውም ብለዋል፡፡

እንደ አብነትም ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አባል አለመሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሆኖም ሀገራችን አባል ባልሆነችበት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ይመክራል፤ ውሳኔ ይሰጣል፤ መግለጫም ያወጣል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በዚህ ተጠቃሚ ሳትሆን ተጎጂ ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባልተደመጠችበትና ባልተናገረችበት ቦታ ላይ ስለኛ ጉዳይ መምከር አይጠቅመንምም ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ቢቻል ኢትዮጵያ አባል ሆና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሁላችንም ይጠቅማል ብለን መናገር ነበረብንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጥያቄ መሆን ያለበትም እንዴት በተለያዩ ህብረቶች አባል በመሆን የኢትዮጵያን ጥቅም እናስከብራለን የሚል መሆን እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በመጠቀም ሌሎችን መጉዳት አትፈልግም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.