Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ13ኛው የዩኔስኮ የወጣቶች ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በ13ኛው የተመድ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ወጣቶች ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው።

ፎረሙ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የወጣቱ ሚና ላይ በትኩረት እየመከረ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ የወጣቶችን ፖሊሲ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ጠቁመው፥ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ለወጣቱ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ እንዲሁም አስከፊ ስደትን ለማስቀረት ከሀገራት ጥረት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ተቋማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር ወጣቱን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስትሯ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከሞሮኮ ወጣቶች ባህልና ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር መሂድ ቤንሰይድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በወጣቶች ዙሪያ የሚሠሩ ስራዎችን በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው የፓን አፍሪካ ወጣቶች ፎረም ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.