Fana: At a Speed of Life!

ሠራዊቱ በጥቃቅን ችግሮች እንዳይጠመድ የፖለቲካ አመራሩ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት አለበት – ዲማ ነጎ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጥቃቅን ችግሮች እንዳይጠመድ የፖለቲካ አመራሩ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነጎ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ቋሚ ኮሚቴው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።
በወቅቱም የፖለቲካ አመራሩ የፖለቲካ ስራዎችን በመስራት ሠራዊቱ ከጥቃቅን የፀጥታ ችግሮች እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባው ዶክተር ዲማ አስገንዝበዋል።
ሠራዊቱ የሀገሪቷ የመጨረሻ ምሽግ መሆኑን ተረድቶ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።
ሠራዊቱ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ለሕገ-መንግስቱ ያለውን ታማኝነት በቀጣይ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ከፍተኛ ሚና በማውሳትም ሠራዊቱ የተለመደውን ብቃቱን እንዲወጣ ለስምሪት የሚላኩ የሠራዊት አባላት ምልመላ አሠራር ግልፀኝነት እንዲኖረው መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቀበሌ፣ የወረዳና የዞን አስተዳደሮች የፀጥታ ስራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸው ሠራዊቱ በየሰፈሩ እና በየቀበሌው ለጥቃቅን ስራዎች እየተሰማራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሠራዊቱ ለሀገሩ ሉዓላዊነት መከበር ትልቅ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ በጽንፈኛ ኃይሎች ያለ ስሙ ስም እየተሰጠው ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተበት አብራርተዋል።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሀገሩን ሠራዊት ደፍሮ የሚሳደብና የሚያጥላላ አካል አለመኖሩን ገልጸው፤ በሠራዊቱ ላይ የማጥላላትና የስድብ ዘመቻ በከፈቱ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ገልፀዋል።
ሀገርን ለመበተን የሚሰሩ ኃይሎች በሠራዊቱ ላይ የከፈቱትን ማጥላላት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ ከሠራዊቱ ጎን ሊሰለፍ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.