Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 3 ወራት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ፓስፖርት ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ፓስፖርት ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ባለፉት 3 ወራት ውስጥ የተሰሩ ስራዎችን በሚመለከት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ሦስት ወራት 531ሺህ 800 ፓስፖርት ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል።

ፓስፖርቱ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባለፈው ሶስት ወር ከፓስፖርት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን በመፍታት ከስድስት ወር በላይ በመጠበቅ ላይ ላሉ ዜጎች ፓስፖርት እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል።

በዚህም ለአዲስ አበባ ከተማ አመልካቾች ቅድሚያ በመስጠት 45 ሺህ 366 ፓስፖርት መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

በዋናነት በሶስት ወሩ አዲስ አበባ ላይ ላሉ ደንበኞች ሲሰጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ለክልል ደንበኞችም ፓስፖርት የመስጠት ስራ ተጀምሯል ተብሏል።

በዚህም 8 ሺህ 500 ፓስፖርት ለክልሎች ተሰራጭቶ ለደንበኞች በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ፓስፖርት የታተመላቸው ዜጎች በግል ስልካቸው መልዕክት በመላክ ፓስፖርታቸውን እንዲወስዱ እየተደረገ እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡

ቅድሚያ የሚሰጣቸውም የስራ ስልጠና ወስደው በውጭ የስራ ዕድል ላገኙ እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል።

በውጭ ለሚኖሩ 40 ሺህ 531 ለሚሆኑትም ፓስፖርት በ3 ወር ውስጥ መስጠት ተችሏልም ተብሏል።

በመሳፍንት እያዩና በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.