Fana: At a Speed of Life!

የባህር በር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መቃኘት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 7 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የባህር በርና የወደብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መመልከት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ አመለከቱ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት “ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ የፍትሐዊ ወደብ አጠቃቀም ልዩ ሴሚናር እየተካሄደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ተደራዳሪ ቡድን አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ያለውን አንድምታ አስመልክቶ የመወያያ ጸሑፍ በልዩ ሴሚናሩ ላይ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ጥያቄና ፍላጎት የረጅም ጊዜ የታሪክ መሰረት እንዳለው ያነሱት አምባሳደር ኢብራሂም፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት የባህር በርና ወደቦችን በሰጥቶ መቀበልና የሀገራትን ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ መጠቀም መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀገሪቱ ፍላጎት ዓለም አቀፍ ሕግን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እ.አ.አ በ1982 የፀደቀውን ዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር በመነጋገር ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡባቸውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ኢትዮጵያ መመልከት እንዳለባትም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የባሕር በር የሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት የሚያነሷቸውን የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባና ቀጣናዊ ተቋማት ለጉዳዩ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በተመለከተም እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውይይቶችን በማዘጋጀት ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የቀጣናው ሀገራት ምሁራን ለመንግስታት ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች መሰረት የሚጥሉ ተከታታይ ምክክሮችን በማድረግ የመፍትሔ አማራጮችን እንዲያመላክቱም ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.