Fana: At a Speed of Life!

የመስኖ መሰረተ ልማትን ለመደገፍ የሚያስችል ውይይት ከኤግዚም ባንክ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተካሄደ

 

አዲስ አበባ፣ ኅዳር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድ የተመራ ልዑክ ከደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ ኤግዚም ባንክ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሚኒስቴሩ ለማከናወን የታቀዱትን ፕሮጀክቶች ሊደግፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሃመድ÷ ኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ10 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ እንዲሁም ከፍተኛ የውሃ እምቅ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በቁጠባና በውጤታማነት እየተጠቀመችበት አለመሆኑን ገልፀው፤ በዚህም በተደጋጋሚ በድርቅና በጎርፍ አደጋ እንደምትጠቃ ተናግረዋል።

ላለፉት አራት አመታትም በምግብ ራስን ለመቻል በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ ጠንክራ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም ለመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ብድር ከባንኩ ማግኘት እንፈልጋለንም ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የባንኩ ዋና ዳይሬክተር ኪ-ዩን ሂዋንግ÷ በተለይም የቦረና እና ሱሉልታ ከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማትን ባንኩ እንዲደግፍ የጥናትና ዲዛይን ዶክመንቶችን መጠየቁን ጠቁመዋል።

የቀረቡትን ሰነዶች አይተን የባንኩን መስፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውን አረጋግጠን የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታን መደገፋችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.