Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲቢኢ ኑር ደንበኞች ጋር ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲቢኢ ኑር ደንበኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል አንዱ አካል ሆኖ በተከታታይ የሚካሄደው የደንበኞች ምክክር በዛሬው እለት “ስኬታማ ምዕራፍ፤ ብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ÷ በምክክር መድረኩ ላይ በመገኘት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የተጀመረበትን ሂደት፣ ባንኩ ከ20 ዓመት በፊት በእምነታቸው ምክንያት ከባንክ የራቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን የባንክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረጋቸውን ጥረቶችና አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ ያሳለፈውን ሂደት አብራርተዋል፡፡

መድረኩ ከባንኩ ጋር አብረው ለሚሠሩ ደንበኞች ምስጋና ለማቅረብ እና በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የደንበኞችን አስተያየት ለመቀበል መዘጋጀቱንም ገልፀዋል፡፡

ከባንኩ ጋር የሚሠሩ የሲቢኢ ኑር ደንበኞች ይሻሻሉ፣ ይስተካከሉ ያሏቸውን ጉዳዮች በመድረኩ ያነሱ ሲሆን÷ አቶ አቤ ሳኖ፣ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን እና የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ሞሀመድ ዘይን ኑር (ዶ/ር) ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ ተገኝተው በውይይቱ የተሳተፉ የባንኩ ደንበኞች “እንኳን ለ10ኛ ዓመት የሲቢኢ ኑር ክብረ በዓል አደረሳችሁ” መልእክት አስተላፈዋል፡፡

ባንኩ በእምነት ምክንያት ከባንክ የራቁ ደንበኞችን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ላደረገው ጥረት እና እየሠራ ላለው ጠንካራ ሥራ ምስጋና ማቅረባቸውን ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ ገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባላት፣ ደንበኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.