Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዒድ አልፈጥር መልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለእስልምና አምነት ተከታዮች የ1441ኛው የዒድ አልፈጥር ክብረ በዓል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ።

አቶ ደመቀ በመልዕክታቸው “በዘንድሮው ታላቁ የረመዳን ወር በፆም የዘለቅነው ሲሆን፥ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ በመመካከር፣ በመደጋገፍ እና በመረዳዳት መልካም ጊዜ አሳልፈናል” ብለዋል።

በታላቁ የረመዳን ወር በሃገሪቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስቀድሞ ከመከሰቱ ጋር በተያያዘ የአምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን በመጠበቅ እንዲሁም ለሌሎች ወገኖች በመጠንቀቅ አስተውሎት በተሞላበት አግባብ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

“በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የመደጋገፍ እና የጥንቃቄ ልምምዳችንን ይበልጥ በማፅናት፥ በቀጣይ ጊዜያት ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመግታት እንዲሁም ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት ለመቀነስ የጥንቃቄ መመሪያዎቹን አጠናክረን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል” ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወረርሽኙ ስርጭት አዝማሚያ እየሰፋ መቀጠሉን መረጃዎች እየጠቆሙ መሆኑን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሌሎች ወገኖችም የጥንቃቄ መመሪያዎቹን ሳይዘናጉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከልብ ማበረታታት ይገባልም ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.