Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2015 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

በእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች በተጨማሪ ጥሩ ወጤት ላስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች እና ለክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶችም እውቅና እየተሰጠ ነው።

በከተማ አስተዳደሩ 600 እና ከዚያ በላይ ላስመዘገቡ 97 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች፣ 450 እና ከዚያ በላይ ላስመዘገቡ 66 ተማሪዎች እንዲሁም 6 የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች እና ሶስት ክፍለ ከተሞች እውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በከተማ አስተዳደሩ ሃናን ናጂ በተፈጥሮ ሳይንስ 649 ውጤት በማስመዝገብ በ2015 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ዘርፍ አካላትና አመራሮች እንዲሁም ተሸላሚ ተማሪዎችና ወላጆች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለትምህርት ዘርፉ እድገት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽም ለዚሁ ውጤታማነት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ምዕራፍ የእናንተ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁም ውጤታማ በመሆን እራሳችሁንና ቤተሰቦቻችሁን እንዲሁም ሀገራችሁን እንድትጠቅሙ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ተማሪዎች በቀጣይ ተግተው በመስራት ውጤታማ እንደሚሆኑ እምነት አለኝ ብለዋል።

 

በሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.